ኢትዮጵያ ተመድ ሩስያ ለዩክሬን ካሳ እንድትከፍል ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመቃወም ድምጽ ሰጠች
የውሳኔ ሃሳቡን ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት የተቃወሙት ሲሆን 73 ሀገራት ደግሞ ድምፅ ከመስጠት ታቅበዋል
ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሀገራት ያልደገፉት የውሳኔ ሀሳብ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጎታል
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ማምሻውን በሩስያ ላይ ያቀረበው አዲስ የውሳኔ ሃሳብ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት ሩስያ በዩክሬኑ ጦርነት ላደረሰችው ጉዳት ካሳ እንድትከፍል የሚያስገድደውን የውሳኔ ሀሳብ ተቃውመውታል።
አረብ ኤሚሬትስን ጨምሮ 73 ሀገራት በድምፀ ተአቅቦ ማለፋቸውን ተከትሎም የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የመንግስታቱ ድርጅት ካወጣቸው አምስት የውሳኔ ሀሳቦች ሁሉ ይሁንታ የተነፈገው ሆኖ ተመዝግቧል።
የውሳኔ ሀሳቡ በጦርነቱ ለተገደሉና ለቆሰሉ ዩክሬናውያን ሞስኮ ካሳ እንድትከፍል የሚጠይቅ ነው።
በጦርነቱ የጠፋውን የሰው ህይወትና የደረሰውን የንብረት ውድመት የሚያጣራ አለም አቀፍ ቡድን እንዲዋቀርም ተመላክቷል በዚሁ የውሳኔ ሀሳብ።
ዩክሬን - "የውሳኔ ሃሳቡ ፍትህ ለማስፈን ትልቅ ተስፋ ነው"
በመንግስታቱ ድርጅት የዩክሬን አምባሳደር ሰርጌ ኪይልይስታይ፥ ሩስያ ዩክሬንን ለማፈራረስ የመጨረሻ አቅሟን ተጠቅማለች ብለዋል።
"ከመኖሪያ ህንፃዎች እስከ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ያላፈራረሰችው የህዝብ ተቋም የለም፤ ባለፈው ወር ብቻ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ጥቃት አድርሳ ግማሽ ዩክሬን በጨለማ ተውጧል" ነው ያሉት አምባሳደሩ።
የሩስያ ወታደሮች ይዘዋተው በቆዩ የዩክሬን ከተሞች የፈፀሟቸውን ወንጀሎችም በማንሳት ሞስኮ ተጠያቂ እንድትሆን የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አድንቀዋል።
ዩክሬንን መልሶ የመገንባቱ ስራ ሲካሄድ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የመካስ እና ፍትህን የማስፈኑ ጉዳይም እኩል ሊካሄድ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ኬቭ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ሳትጨምር ሳትቀንስ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይፋ ለማድረግ መዘጋጀቷንም በመጥቀስ የውሳኔ ሃሳቡን ፍትህን ለማስፈን የተስፋ ብርሃን ነው ብለውታል።
ሩስያ - "የውሳኔ ሀሳቡ ህጋዊ ያልሆነና ተፈፃሚነት የሌለው ነው"
በመንግስታቱ ድርጅት ሩስያን የወከሉት ቫስሊ ንቤንዚያ በበኩላቸው፥ የውሳኔ ሀሳቡ በአለም አቀፉ ህግ ተቀባይነት የሌለውን ነገር ህጋዊ ለማስመሰል የሞከረና ተፈፃሚነት የሌለው ነገር ነው በሚል ተቃውመውታል።
ምዕራባውያን እንዳይንቀሳቀስ ያገዱትን በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር የሩስያ ሃብት ለመዝረፍ የተቀነባበረ ነው፤ የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤም ይህን ዘረፋ እንዲሸፍንላቸው የውሳኔ ሃሳቡን አቀርበዋል ሲሉም ሀገራት እንዲቃወሙት ጠይቀዋል።
የውሳኔ ሀሳቡን ማፅደቅ የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ አምራቾችን ከመጥቀምና አለምን የባሰ ውጥረት ውስጥ ከመክተት ውጭ ፋይዳ እንደሌለውም አስገንዝበዋል።
ቻይና፣ ኢራን፣ አንጎላ፣ ቬንዙዌላን ጨምሮ 16 ሀገራት ለሩስያ ድጋፋቸውን በፊርማ ገልፀው፥ ፍትህ በተገቢው የህግ ስርአት እንጂ ምንም አይነት የህግ መሰረት በሌለው የውሳኔ ሃሳብ አይደለም ብለዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ያላት ሩስያ የሚቀርቡባትን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርጋለች።
በጠቅላላ ጉባኤው ግን ይሄው ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን የላትም፤ ይሁን እንጂ የጠቅላላ ጉባኤው የውሳኔ ሃሳብ እንደ ፀጥታው ምክርቤት ህጋዊ አስገዳጅነት የለውም።
በካናዳ፣ ጓቲማሚላ፣ ኔዘርላንድና ዩክሬን አነሳሽነት የቀረበው የትናንቱ ሩስያ የጦር ካሳ ትክፈል የውሳኔ ሀሳብ በ94 ሀገራት ድጋፍ ቢፀድቅም በሞስኮ ላይ ህጋዊ ጫና አያመጣም።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ባስተላለፉት የቪዲዬ መልዕክት ግን ሩስያ ላደረሰችው ኪሳራ ሁሉ ካሳ መክፈሏ ከይቀሬ ነው ብለዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው፥ እንዳይንቀሳቀስ ያገዱትን የሩስያ ሃብት በካሳ ስም ለዩክሬን ለመስጠት ላሰቡት ምዕራባውያን የትኛውንም ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ዝተዋል።