ተመድ ለሩሲያ “ከፍተኛ ተግሳጽ” ነው የተባለውን የውሳኔ ሃሳብ አጸደቀ
ሩሲያ የውሳኔ ሃሳቡ "ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን የሚያዳክም ነው"ብለዋለች
አሜሪካና ዩክሬን የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ሩሲያ ዓለም ማስፈራራት እንደማትችል ያሳየ “አስደናቂ ውሳኔ” ነው ብለውታል
የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የዩክሬን ግዛቶችን “በኃይል ጠቅልላለች” ያላትን ሩሲያ አወገዘ፡፡
በትናንትናው እለት በተካሄደው ጉባኤ ሩሲያ አራት የዩክሬን ክልሎችን መጠቅለሏን ተከትሎ የጸጥታው ም/ቤት "ህገ-ወጥ" ነው ለተባለው ህዝበ ውሳኔ እውቅና እንዳይሰጥና ሩሲያ ጦሯን ከዩክሬን ምድር እንድታስወጣ የሚያስገድድ የውሳኔ ሃሳብ በከፍተኛ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በዚህም መሰረት ከ193 አባላት ጠቅላላ ጉባኤ ውስጥ ሶስት አራተኛው ወይም 143 ሀገራት የዩክሬንን ሉዓላዊነት ፣ ነጻነት ፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ድንበሮች ውስጥ ያጸደቀውን ውሳኔ ደግፏል ።
ውሳኔውን ተከትሎ ተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ፤ውጤቱ ሩሲያ ዓለምን ማስፈራራት እንደማትችል ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የዩክሬን አምባሳደር ሰርጊ ኪስሊቲስ በበኩላቸው "በጣም አስደናቂ ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች መናገራቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡን በመቃወም አራት ሀገራት ቤላሩስ ፣ ኒካራጓ ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሶሪያ ሩሲያን የተቀላቀሉ ሲሆን ሌሎች ቻይና፣ ህንድ፣ ፓኪስታን እና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙባቸው 35 ሀገራት ጨምሮ ድምጽ ተአቅቦ አድገዋል እንዲሁም የተቀሩት ምንም አቋም ሳያንጸባርቁ ወጥተዋል።
ውጤቱ ጠቅላላ ጉባኤው የሩስያ ወታደሮች እንደፈረንጆቹ የካቲት 24 በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ በኋላ ካጸደቃቸው አራት የውሳኔ ሃሳቦች አንጻር ሲታይ ለሩሲያ “ ከፍተኛው ተግሳጽ” ነው ተብሏል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የጉባኤውን ውሳኔ አሞካሽተው ድምጽ ለሰጡ ሀገራት ምስጋና አቅርበዋል።
“ዩክሬን እያንዳንዷን ኢንች መሬት ታስመልሳለች” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አስፍረዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
“ሩሲያ እንዲሁ በዘፈቀደ ሉአላዊ ግዛቶችን ከዓለም ካርታ መፋቅ እንደማትችል ያሳየ ውሳኔ ነው” ያሉት ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ናቸው፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ ከድምጽ መስጫው በፊት ለጠቅላላ ጉባኤው እንደተናገሩት የውሳኔ ሃሳቡ "ፖለቲካዊ እና ተንኳሽ" መሆኑን በመግለጽ "ለችግሩ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄን የሚደግፉ ሁሉንም ጥረቶች ሊያጠፋ ይችላል" ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የቻይናው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል አምባሳደር ጄንግ ሹንግ በበኩላቸው ቻይና ውሳኔው ጠቃሚ ነው ብላ እንዳማታምን ተናግረዋል፡፡
"በጠቅላላ ጉባኤው የሚወሰደው ማንኛውም እርምጃ ሁኔታውን ለማርገብ፣ ውይይትን የሚያበረታታ እና ለዚህ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያመጣ መሆን አለበት" ሲሉም አክለዋል አምባሳደሩ፡፡