ሩሲያ በፌደራል መንግስትና ህወሃት ድርድር ጉዳይ የአፍሪካ ህብረትን እድግፋለሁ አለች
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የጀመረው ጥረት እንደምትረዳም ሩሲያ አክላለች
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሃት ዙሪያ ስለሚደረገው ድርድር መግለጫ ሰጥቷል
ሩሲያ በፌደራል መንግስት እና ህወሃት ድርድር ጉዳይ የአፍሪካ ህብረትን አቋም እድግፋለሁ አለች።
በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ እና ፕረስ ምክትል ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ኢቫን ኔቻዬቭ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
- መንግስት ከህወሃት ጋር ድርድር የሚካሄድበትን ቦታ ለመወሰን ከአፍሪካ ህብረት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስታወቀ
- ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ162 ሚሊዮን ዶላር ብድር እዳ ሰረዘች
በአዲስ አበባ ያለው የሩሲያ ኢምባሲ መግለጫውን ለተከታዮቹ ያጋራ ሲሆን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተካሄደበት ያለውን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እያደረገው ያለውን ጥረት ሩሲያ በአወንታዊንት እንደምትቀበለው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁ፣ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑ እና ሌሎች የሰላም አማራጮች እየተከተለ መሆኑ ግጭቱን ለማስቆም ጥሩ እርምጃ መሆኑንም ሩሲያ አክላለች።
እንዲሁም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ይፋ ያደረጉት ከህወሃት ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑ ሌላኛው መልካም ነገር መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከህወሃት ጋር የተደረገውን ጦርነት ለመፍታት እየሄደችበት ያለውን ሂደት እንደምታደንቅ የገለጸችው ሩሲያ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ኦልሴጎን ኦባሳንጆ በኩል እየተካሄዱ ያሉ ጥረቶችን እንደምትደግፍም ገልጻለች።
መንግሥት ከህወሃት ጋር ያደርገዋል የተባለው ንግግር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ብቻ እንደሆነ እንዲሁም ድርድር የሚካሄድበትን ቦታ ለመወሰን ከአፍሪካ ህብረት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
ህወሓት በበኩሉ በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ፤ የአፍሪካ ሕብረት ከኦባሳንጆ ይልቅ፤ ኡሁሩ ኬንያታን ወይም ታቦ ኢንቤኬን ወይም ሌላ ሰው ከሰየመ ችግር እንደሌለበት ገልጿል።
ህወሓት በኬንያ ድርድር ለማድረግ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።
ቻይና ከዚህ በፊት የፌደራል መንግስትን እና ህወሃትን ለማደራደር ፍላጎት እንዳላት መናገሯ ይታወሳል።