የፌደራል መንግስትና እና ህወሓት ግጭቱን በድርድር መፍታት እንደሚፈልጉ በተናጠል አስታውቀዋል
በትግራይ ክልል የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ በህወሃት መጠቃቱን ተከትሎ ነበር ወደ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጦርነት የተጀመረው፡፡
ይህ ጦርነት ጥቅምት 2013 ዓ.ም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ቁጥሩ በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተውበታል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትግራይን እስከ ተቆጣጠረበት እና ከትግራይ ለቆ ከወጣ ጊዜ በኋላ በተካሄዱት የሁለት ዙር ጦርነቶች ከሰው ልጆች ህይወት መጥፋት ባለፈ ለዘመናት የተገነቡ የተቋማት መሰረተ ልማት ሲያወድሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችንም ለእርዳታ የዳረጋቸው ሲሆን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለከፍተኛ ስጋት እና የውጭ ተጋላጭነቷን የበለጠ አስፍቶታል፡፡
በርካቶች ሶስተኛ ዙር ጦርነት እንዳይጀመር ስጋታቸውን ቢገልጹም ሌሎች ደግሞ ጦርነቱ እንዲቀጥል እና አሸናፊነት እንዲረጋገጥ በተለያዩ መንገዶች ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል፡፡
አሁን ላይ ሁለቱም አካላት ግጭቹን በሰላም ለመፍታት እንደሚፈልጉ በተናጠል አሳውቀዋል፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለድርድር መዘጋጀታቸውንም ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ያየህ ገነት ለአል ዐይን አማርኛ እንደታናገሩት ከጦርነት በፊት ድርደሩ ቢካሄድ ሁሉም አትራፊ ይሆኑ ነበር፡፡
በአንድ ህዝብ መካከል እና በተመሳሳይ በጀት የሚካሄድ ጦርነት አሻናፊ የማይኖርበት ጦርነት ነው ብለዋል መምህሩ፡፡ጉዳዩ በድርድር መፈታት የነበረበት ነበር ያሉት መምህሩ አሁንም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር መምጣታቸው ቢዘገዩም ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ አካላት በአደራዳሪው አካል ላይ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው የድርድሩ ዋነኛ ስጋት ነው የሚሉት መምህር ያየሕ ህወሃት ኬንያ በተለይም ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያደራድሩን ሲል የፌደራል መንግስት ደግሞ ድርድሩ አፍሪካ ህብረት ያደራድረን ማለታቸው መቋጫ ሊኖረው ይገባልም ብለዋል፡፡
መምህሩ ያየህ ኬንያ የምዕራባዊያን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ተቋማት ማዕከል በመሆኗ እና ሕወሃት እነዚህን ለመጠቀም ሲል ነው ድርድሩ በናይሮቢ ይሁን ያለው ሲሉም አክለዋል፡፡
ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ቅድመ ሁኔታ መደርደር ሳይሆን ሁለቱም አካላት ሰው እንዳይጎዳ በተቻላቸው አቅም ተባባሪ መሆን እና ብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መጠንቀቅ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ውስጥ ከማስገባቱ ባለፈ የዲፕሎማሲ መንገራገጭ አጋጥሟታል፣ ድርድሩ እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንድትፈታ ያግዛልም ብለዋል፡፡
ድርድሩ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ስጋትን የሚፈጥር መሆን የለበትም፣ በአጭር ጊዜ እና በረጅም ጊዜ የሚፈታ መሆን አለበት፡፡ በተለይም የይገባኛል በሚል ጥያቄ የሚነሳባቸው መሬቶች ጉዳይ፣ የታጣቂዎችን ጉዳይ በዋናነት መፍትሄ መስጠት ይኖርበታል ሲሉም ለተደራዳሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኬንያ ገለልተኛ አትሆንም ከኬንያ ጀርባ ራሷን ጨምሮ የብዙ ሀገራት ፍላጎት አለ፣ የአፍሪካ ህብረትም አስተማማኝ ባይሆንም በአንጻራዊነት የአፍሪካ ህብረት ድርድሩን ቢመራው ለኢትዮጵያ የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑም ረዳት ፕሮፌሰር ያየህ ተናግረዋል፡፡
የምእራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ፍላጎት በፌደራል መንግስት እና በህወሃት መካከል ሊደረግ የታሰበው ድርድር ዋነኛ ወሳኝ ነገር እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ በጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ህግ መምህር ሰለሞን ጓዴ ናቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ህወሃት በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚጋፋ መንገድ በግልጽ መግለጫዎችን ሲያወጡ እና ህወሃትን በመረጃ እና በፕሮፓጋንዳ ሲደግፉ ቆይተዋልም ብለዋል፡፡
ህወሃት በታሪኩ በድርድር ሲቀበል የመጣ እንጂ በሰጥቶ መቀበል መርህ የማያምን ድርጅት ነው የሚሉት ሰለሞን ህወሃት የፌደራል መንግስትን አቅም አይቶ ወይም ምርጫ አጥቶ ካልሆነ በስተቀር ሊደረግ በታሰበው ድርድር እስከ መጨረሻው ሊሳተፍ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ ወደ መቀሌ ያቀኑት የምዕራባዊያን አምባሳደሮች ዋና አላማ ሰላም ስለሚመጣበት መንገድ ለመነጋገር ሳይሆን የሕወሃትን አቅም ለመሰለል ወይም የመዋጋት አቅምን ለማየት እንደሄዱ ስጋት እንዳላቸውም መምህሩ አክለዋል፡፡
ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ጦርነት እንዳይጀመር ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ ህወሃት ተገዶ ወደ መቀሌ በተጓዘበት ወቅት እና ጦርነት እንደሚጀምር በተለያዩ መንገዶች ሲናገር ጫናዎችን በማድረግ ከፌደራል መንግስት ጋር ወደ ሰላም እንዲመጣ ማድረግ ይችሉ እንደነበርም ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ጦርነቱ የተጀመረው በነዚሁ ምዕራባዊያን ፍላጎት እንደሆነ የተናገረው መምህር ሰለሞን ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆንም የምዕራባዊያን ፍላጎት ዋነኛው ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳይ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው የድርድሩ ስጋት የፌደራል መንግስት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ እና በአገር ውስጥ ምክንያቶች በሚፈጠሩ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና ሌሎች ጫናዎች ምክንያት ድርድሩ ላይ ስህተት ሊሰራ እንደሚችል ስጋት አለኝ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የፌደራል መንግስት እና ህውሓት በተናጠል በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በድርድር ለመቋጨት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ለመደራደር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ቡድን መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀረቡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል
ህወሓት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ለመደራደር መፈለጉን ከመግለጻቸው ቀደም ሲል በኬንያ አስተናጋጅነት እና አመቻችነት ለሚደረገው ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልፆ ነበር፡፡መንግስት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ብቻ ይመራ ሲል ህወሓት ግን በዚህ እንደማይስማማ ገልጿል፡፡