በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረው ጦርነት እስካሁን እልባት አለማግኘቱ የታቀደውን ምክክሩ ድርድር እንደሚያስመስለው ምሁራን ይናገራሉ
መንግስት የልዩነት ምንጭ በሆኑና በሚያወዛግቡ የጋራ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ያስፈልጋል በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ ምክክርን ለማድረግ መወጠኑን ካስታወቀ ዋል አደር ብሏል፡፡
ለምክክሩ መቀላጠፍ እና ከግብ መድረስ ይበጃሉ ያላቸውን ወሳኝ እርምጃዎች ሲወስድም ነበር፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በአዋጅ ደንግጎ ከማጽደቅም ባለፈ የእጩ ኮሚሽነሮች ምርጫ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊ እና አካታች እንዲሁም ተዓማኒ እንዲሆን በሚል መንግስት በከባድ ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል አስሯቸው የነበሩ ሰዎችን መልቀቁም ይታወሳል፡፡
በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣በፖለቲካኛ ጃዋር መሃመድ መዝገብ የነበሩ ሰዎችን እና አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የህወሓት አመራሮች በመንግስት ውሳኔ ከእስር ፈትቷል፡፡
ነገርግን መንግስት በትግራይ ክልል ባደረገው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ወቅት ከሸሹበት በረሃ አድኖ፣ አዲስ አበባ አምጥቶ ያሰራቸው በሽብር የተፈረጀው የህወሓት አመራሮችን መለቀቅ በበጎ ያልተቀበሉት ብዙ ናቸው፡፡ እንዴት ለጦርነት ምክንያት የነበሩ ሰዎች ይፈታሉ የሚሉ ጥያቄዎች በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ተነስተዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ስለ ውሳኔው የፍትሕ ሚኒስትሩን ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ን አግኝቶ ለመጠየቅ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለኢዜአ በሰጡት ቃል ምልልስ መንግስት ክስ በማቋረጥ እስረኞችን ለመልቀቅ የወሰነው ሀገራዊ ምክክሩን አካታች ለማድረግ አስቦ ነው በማለት የውሳኔውን ምክንያታዊነት ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ልሂቃን አልፎ ወደ ማህበረሰቡ እየተንጸባረቁ ያሉ አለመግባባቶችን ከመደበኛው ፍትህ በተጨማሪ የተሃድሶ የሽግግር ፍትህ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ ሚኒስትሩ በዚሁ ቃል-ምልልስ ሀገራዊ መግባባት እና መስማማት የሚያስፈልግባቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እስካሁን ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር አልተደረገም፤ይሄ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ብለዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ስለ ጉዳዩ ያነጋገራቸው የህግ ምሁራንና ባለሙያዎች ግን በሽግግር ጊዜ እና በተሃድሶ ፍትሕ ጭምር ተደግፎ ይፈጸማል ስለተባው ብሔራዊ ምክክር ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ይደረጋል የተባለው “ብሔራዊም ምክክር” ምክክር ነው ወይስ ድርድር ሲሉ ያነጋገርናቸው ምሁራን ይጠይቃሉ፡፡
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ አለሙ ጦርነቱ ሳያልቅ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋም፤ ምክክሩ ድርድር እንዲመስል ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም አሁን ላይ ያለው መንግስት “ለስሙ ፓርቲ ቀየሮ ብልጽግና መባሉና አመራር ላይ ያሉት ሰዎቹ አዲስ አለመሆናቸው፤ ሕዝብ ጉዳዩን በጥርጣሬ ሊመለከተው እንደሚችል” አቶ አለሙ ይገልጻል፡፡
ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሁር ብሔራዊ ምክክር ሀገርን ለመታደግና ለማዝለቅ በሚል የሚደረጉ እንዲህ ዐይነት እርምጃዎች ለውጥ ወይም የተለወጠ ስርዓት ባለበት ሁኔታ ውስጥ የሚፈጸሙ ናቸው ይላሉ፤ አሁን የተለወጠ ነገር እንደሌለና የፖለቲካ ተዋናዮቹ ቀደም ሲልም የነበሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
ስለዚህ “ሊሆን የሚችለው በዋናዎቹ፤ ኃይልና ጉልበት ባላቸው የፖለቲካ ኃይሎች መካከል፤ የተሻለ ፖለቲካዊ ባርጌይን ለማግኘት የሚደረግ ድርድር እንጂ ምክክር አይደለም” ይላሉ ምሁሩ፡፡
“ጦርነቱ በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኝ አይመስለኝም፤ ያግኝ እንኳ ቢባል በአጭር ጊዜ የሚሳካ አይነት አይመስልም፡፡ ስለዚህ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥል ብሔራዊ ምክክር ይባል እርቅ በውይይት ይፈታ ነው፤ ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ ድርድር ነው ማለት ነው” ሲሉም ነው የሚስቀምጡት ፡፡
ለችግሩ ሊፈለግ የሚችለው መፍትሔ “ፖለቲካዊ ነው” የሚሉት ምሁሩ መንግስትን ጨምሮ ዋና ዋና የችግሩ ተዋናዮች “ሊደራደሩ እንጂ ሊመካከሩ አይቀመጡም፤ ፋይዳ ባላቸውና ኃይል በገነቡ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ለስልጣን ክፍፍል የሚደረግ ድርድር እንጂ ምክክር አይደለም” ሲሉም ይናገራሉ፡፡
ይህም በዋና ዋና የፖለቲካ ተዋናዮች (አክተሮች) መካከል የሚደረግ በመሆኑ የመደራደር አቅምን ይፈልጋል እንደ ምሁሩ ገለጻ፡፡
ብሔራዊ ምክክሩን በተመለከተ የተሰጠ የተብራራና እንደማን እንደሚነጋገሩ እንኳን የታወቀ ነገር አለመኖሩ ወደዚሁ ማደማደሚያ እንደሚያደርስ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን ቀደም ሲል ለሚዲያ በሰጡት ገለጻ የሃገራዊ ምክክሩ ዓላማ ለተወሰኑ ዓመታት የሚያስተዳድር መንግስት ማቋቋም አለመሆኑን፤ ይልቁንም የሀገረ መንግስቱን እጣ ፋንታ በሚወስኑ መሰረታዊ መርሆዎች ላይ መግባባት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ለዚህ በቅድሚያ የልዩነት ምንጭ የሆኑና የሚያወዛግቡ ሃገራዊ ጉዳዮች እንደሚለዩና የሚቋቋመው ኮሚሽን የመጀመሪያ ስራው ይኸው መሆኑንም ገልጸዋል፤ ሰፋፊ ሃገራዊ ውይቶችን ማዘጋጀት ቀጣይ ስራው እንደሆነም መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን ኮሚሽኑ ነጻ ሆኖ የበጀት እና የስራ ዋስትና ነጻነት ኖሮት እንዲቋቋም እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) ሀገሪቱ ጦርነት ላይ ሆና ብሔራዊ ምክክር ይደረጋል መባሉ ምክክሩን ድርድር አያስመስለውም ወይ በሚል ከአል ዐይን አማርኛ ለተነሳላቸው ጥያቄ “ምክከሩ ወደ ድርድር ሊወስደን ይችላል” ብለዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) በቀጣይ ግን ተወያይቶ የሚፈታ ነገር ሊኖር እንደሚችል ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ምክክር ወደ ድርድርና ሰጥቶ መቀበል “ሊወስደን ይችላል” ብለዋል፡፡
በምክክሩ ሂደት ላይ ከሚያጋጥሙን ነገሮች አንዱ ድርድር ሊሆን እንደሚችልም ነው ሰብሳቢዋ ያነሱት፡፡
በሀገራዊ ችግሮች ላይ ውይይት፣ መመካከርና መነጋገር ሲጀመር ወደ ድርድር ሊወስድ እንደሚችል ገልጸው ከዛ በኋላ ግን ድርድር አስፈላጊ ከሆነ ወደዛው መሄድ እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡ ጦርነቶችና መፈናቀሎችን የሚያመጡት ስር የሰደዱ ምክንያቶች እንደሆኑ ያነሱት ሰብሳቢዋ እነዚህ ችግሮች ግን ድርድር ጋር ሳይደረስ ሊፈቱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በህዝብ እና በፖለቲካ ልሂቃን መካከል መግባባት ለመፍጠር እንጅ በሽብርተኝነት ከተፈረጁት (ህወሓት እና ሸኔ) ጋር ለመደራደር አለመሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ምክክሩ ህገመንግስት እና ሰንደቅ አላማን ጨምሮ በሌሎች በዋናዋና ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ነው ብሏል፡፡
ህወሓት ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ከመንግስት ጋር በሌላ አካል በኩል እየተነጋገረ መሆኑን ቢገልጽም፣ መንግስት ግን ከህወሓት ጋር ድርድርም ሆነ ንግግር አልጀመርኩም ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል፡፡
የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው፤አሜሪካም በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገውን ጥሪት እንደምትደግፍ ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ምክንያት ሆኗል፡፡