ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ “ድርድር” ምን አሉ?
“ከአሸባሪ ጋር ድርድር አይካሄድም የሚለው አባባል በደምብ ማየቱ ጥሩ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስተሩ “ለጦርነት የምንወስነው በብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ብቻ ነው ፤ከዛ በመለስ ግን በራችን ለሰላም ክፍት ነው”ም ብለዋል
በዛሬው እለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከህዝብ እንደራሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቆዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድርድርን በተመለከተ የመንግስታቸውን እና የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉትን አቋም ግልጽ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚነሲትሩ፤ድርድርን በተመለከተ ከአንድ የምክር ቤቱ አባል የቀረበላቸውን ጥያቄ በመንተራስ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ምርጫ አሁንም ለሰላም ቅድሚያ መስጠት መሆኑ ተናግረዋል፡፡
“ለጦርነት የምንወስነው በብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ነው፤ የኢትዮጵያ አንድነትና ጥቅም በሰላም መንገድ ማስጠበቅ ሲሳነን የህይወት ዋጋ መስዋእትነት እንከፍላለን፤ ከዛ በመለስ ተስፋ አለ ብለን ካሰብን ደግሞ በራችን ለሰላም ክፍት ነው”ም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ድርድርን በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግስት የሚመራው ብልጽግና የመወሰን ህጋዊ ስልጣን እንዳለውና ያስታወሱ ሲሆን ፤ነገር ግን ንግግሩ ይሳካል አይሳከም የሚለው ጉዳይ በሂደት ሚታይ መሆኑም አስረድተዋል፡፡
“ከአሸባሪ” ጋር ድርድር አይካሄድም የሚለው አባባል በደምብ ማየቱ ጥሩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በውጊያዎች መሃል በየትኛውም ዓለም ድርድር የተለመደ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
“ደርግ ሁሉ ጊዜ ከኤርትራ ህዝባዊ ግንባር(ህግኤ) እና ህወሐት ይደራደር ነበር፤ ሁቲዎች አቡዳቢ ሮኬት እየተኮሱ ይደራደሩ ነበር፤ ይነገርም አይነገርም ውጊያ ውስጥ ሁሌም ድረድር ይካሄዳል፤ ድርድር የሚካሄደው ከድርድር ውስጥም ትርፍ ካለ ለማግኘት ነው” ሲሉም በአብነት አንስተዋል፡፡
አሁን ባለው ኢትዮጵያ ሁኔታ በንግግር የሚፈታ ነገር ካለ ማየቱ ግን ጉዳት እንደሌለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማንኛውም ዜጋ መጠየቅ ያለበት የኢትዮጵያን መንግስት ብሄራዊ ጥቅምን አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ ብቻ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
“በአንድ በኩል ተፈናቀልን፣ችግር አለ፤ሰው ሞተ እያልን በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዱን ነገር በሰላም እንቀንስ ስንል ካልፈቀዳችሁ እንዴት እንፍታው ታዲያ..?” ሲሉም ምክር ቤቱን ጠይቀዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለቸው ከብዙ ሃይሎች እና የተሸለ የፋይናንስ አቅም እና ሚዲያ ካላቸው ብዙ ኃይሎች እንደሆነ መዘንጋት የለበትም ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብርት ማእቀፍ ከህወሐት ጋር ለሚደረገው ድርድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ የሚመራ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ህወሐት በበኩሉ በኬንያ መንግስት አሸማጋይነት የሚካሄድ ድርድር ካለ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡