ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎች ጥናት መደረጉ ተገልጿል
የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የሥራ ዘመኑ ማለቁ የተገለጸው የጀመረውን ስራ ሳይጨርስ መሆኑ ተገለጸ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜው እንዳለቀ የተገለጸው ስራዎቹን ሰርቶ ሳያጠናቅቅ መሆኑን ገለጸዋል።
የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን መራዘም እንደነበረበትና ጊዜው ማለቅ እንዳልነበረበት ቀደም ብሎ ቢገለጽም መንግስት ግን ተቋሙን አፍርሶታል ተብሏል።
የቀድሞው ኮሚሽን በ 2012 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ጥናት ሰርቶ ማጠናቀቁን ያነሱት ኮሚሽነሩ ይህንንም አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን ጠቅሰዋል። ከወለጋ ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል እና ከጋሞ እና ጎፋ ዞኖች ውጭ በሁሉም ቦታዎች ጥናት ማከሄዱም ተገልጿል።
የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አወል ሁሴን፤ ኮሚሽኑ በስራ ዘመኑ 68 ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ላይ ጥናት ለማካሄድ አቅዶ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፤ በ58 ላይ ጥናት ማድረጉን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል። ቀሪዎቹ ላይ ጥናት ሳይደረግ የኮሚሽኑ ጊዜ አለቀ በመባሉ ጥናቱ አልተካሄድደም ተብሏል።
ኮሚሽኑ ጥናቶችን አጥንቶ ከሕዝብ ጋር መወያየት የነበረበት ቢሆንም ይህንን ሳያደርግ እንዲፈርስ ተደርጓልም ነው የተባለው።
የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በአዋጅ ሲቋቋም በአንዳንድ ወገኖች ሕገመንግሥትን እንደሚጥስ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትንና የክልሎችን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንና ተግባርም እንደሚጋፋ ተቃውሞ ሲቀርብ ነበር።
እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች በመነሳታቸው ወደ ምክር ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ የሕገመንግሥት ጥሰትም ሆነ የምክር ቤቱንና የክልሎችን ሥልጣንና ተግባራትን እንደማይጋፋ በማረጋገጡ ኮሚሽኑ በአዋጅ ጸድቆ በስራ ላይ ቆይቶ ነበር።
ኮሚሽኑ የሥራ ዘመኑ እንዳይራዘም የተደረገው “ህወሃት ስላልፈለገው እንደሆነ ይገለጻል” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽነሩ፤ ህወሃት የኮሚሽኑን መቋቋም እንዳልፈለገው ቢታወቅም የሥራ ዘመኑ ያላተራዘመው “በእሱ ምክንያት ነው ማለት ግን አልችልም” ብለዋል።
የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተቋቋመው የወሰን፣ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ሲቀርቡ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማድረግ በመጨረሻ ግኝት ላይ ተሞርክዞ ለውሳኔ የሚረዳውን ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርብና ድጋፍ እንደሚያደርግ ነበር።
ኮሚሽኑ የተቋቋመው ለምንነትና ወሰን ጥያቄዎች የማያዳግም መፍትሄ የሚሰጥ ጥናት ለማጥናት ነበር።
ኮሚሽኑ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮችን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንደማያስተላልፍም ቀደም ብሎ ተገልጾ ነበር።
ከአስተዳደር ወሰንና ከማንነት ኮሚሽን በተጨማሪም እርቀ ሰላም ኮሚሽንም የሥራ ዘመኑ ሳይራዘም የቀረ ሲሆን መንግስት በሁሉቱ ተቋማት ምትክ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንን አቋቁሟል።