“ራስን በራስ የማስተዳደር አደረጃጀት ወደ ሌላ አደረጃጀት መሸጋገር ያለበት የሕዝብን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ነው” አቶ አደም ፋራህ
“ራስን በራስ የማስተዳደር አደረጃጀት ወደ ሌላ አደረጃጀት መሸጋገር ያለበት የሕዝብን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ ነው” አቶ አደም ፋራህ
የሲዳማ ክልል ይፋዊ የመንግስት ምስረታ ሥነ-ስርዓት በሀዋሳ ተካሂዷል
በኢትዮጵያ አዲስ ክልል ለመመስረት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሔደው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሲሆን በዚህም 10ኛ ክልል ተመስርቷል፡፡
ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ የክልልነት ጥያቄው የተመለሰለት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ይፋዊ የመንግስት ምስረታ ሥነ ስርአት በክልሉ መዲና ተካሂዷል።
በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው የክልሉ መንግስት ምስረታ መርሃ ግብር ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አደም ፋራህን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች ተገኝተዋል፡፡
እጅግ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በታደሙበት እና በሀይቅ ዳር ‘ጉዱማሌ’ ፓርክ በተካሄደው ሥነ-ስርዓት ላይ የሲዳማ ባህላዊ ‘ቄጣላ’ ጭፈራ ተከናውኗል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥቅም እንዲከበር በቀጣይነት እንደሚሰራ ገልጸው፣ አዲሱ የሲዳማ ክልል እንዲጠናከር አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደረግም ቃል ገብተዋል፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ሕገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ 10ኛ ክልል በመመስረቱ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት አቶ አደም የደቡብ ክልልና የቀድሞው የሲዳማ ዞን አመራሮች ይህንን የክልልነት ጥያቄ “በብቃት እንደመሩት” አንስተዋል፡፡ አፈ-ጉባዔው የአዲሱ ክልል አመራሮችም ክልሉን በማቋቋም ሂደት የሰሩት ስራ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ “የለውጡ አመራር የሕዝቡን እውነተኛ ፍላጎት ለማሟላት የገባውን ቃል በተግባር እንደፈጸመ የሲዳማ ክልል ምስክር ነው” ብለዋል አፈጉባዔው፡፡
አንድ አካባቢ ከነበረው የራስን በራስ ማስተዳደር አደረጃጀት ወደ ሌላ አደረጃጀት መሸጋገር ያለበት ለሕዝብ የሚያስገኘውን ተጨማሪ እውነተኛና ትርጉም ያለው ጥቅም ታሳቢ በማድረግ መሆን እንዳለበት አፈ-ጉባዔው ተናግረዋል፡፡
አቶ አደም ለአካባቢ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር እሴት የማይጨምር የአደረጃጀት ለውጥ አላስፈላጊ አስተዳደራዊ ወጭ ከመጨመርና ሕዝቡ አስቀድሞ አግኝቶ የነበረውን ጥቅም ከማሳጣት ውጭ የሚፈይደው አንዳች ነገር እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ የሲዳማ ክልል መንግስት አካባቢው በዞን ደረጃ ከነበረበት ወቅት በተሻለ አቅሙን በመጠቀም ውጤታማና አቅም ያላቸው ክልላዊ ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ “የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ፍትሀዊ የነበረና አፈሙዝ የማይገባው ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም “የለውጡ አመራር የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ምላሽ የሚገባው መሆኑን በማመኑ እውን እንዲሆን አድርጓል” ነው ያሉት፡፡
በሲዳማ ክልል የምስረታ መርሃ ግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ መንግስታቸው ለሲዳማ ክልል መቋቋሚያ የሚሆን 100 ሚሊዮን ብር እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም በሽግግር መንግስቱ ወቅት በወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት አምስት የነበሩ ክልሎች (ከክልል 7 እስከ 11 ያሉት) ከህግ ውጭ ባልታወቀ መንገድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ተሰባስበው ደቡብ ክልል በሚል ስር እንዲካተቱ መደረጉ ይታወሳል፡፡
በደቡብ ክልል ዉስጥ ከሚገኙ ዞኖች አንዱ የነበረው የሲዳማ ዞን ለረጅም ጊዜ የክልልነት ጥያቄውን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ከ 98 በመቶ በላይ የሚሆኑት ድምጽ ሰጭዎች ሲዳማ ክልል ሆኖ እዲደራጅ መርጠዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሲዳማ ከደቡብ ክልል ጋር የመለያየት ሂደቶችን አጠናቅቆ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም የሲዳማ ክልል ከነባሩ የደቡብ ክልል ስልጣኑን መረከቡ ይታወሳል፡፡ በመቀጠልም ሰኔ 27 ቀን 2012ዓ.ም. የሲዳማ ክልል ተመስርቶ ሥራውን መስራት ጀምሯል፡፡