ገዥው ፓርቲ የማንነት ጥያቄዎች የሕዝቡን ነጻ ፍላጎት መሰረት አድርገው እንዲፈቱ ወሰነ
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ውይይጥ አድርጎ መግለጫ አውጥቷል
ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ተገቢው እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ተወስኗል
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ የሚያነሳቸው የማንነት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው ፍትሃዊ የሕዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን እንደሚያምን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ የማንነት ጥያቄዎቹ ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት በማድረግ የሕዝብን ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲሁም የሕዝብን ነጻ ፍላጎት ከግምት ባስገባ መልኩ ሕጋዊ አሰራርን ተከትለው ምላሽ እንዲሰጣቸው አቅጣጫ ማስቀመጡን ኮሚቴው ይፋ አድርጓል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በሀገሪቱ የታየው ለውጥ ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ኢትዮጵያን ከብተና አደጋ ማዳኑንም ፓርቲው ገልጿል፡፡
“ኢትዮጵያን ለመበታተን በከፍተኛ ሁኔታ ተዘጋጅቶ የነበረውን የሕወሓት ቡድን” በማስወገድ ረገድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራና አፋር ክልሎች ልዩ ሃይሎችና ሚላሻዎች እንዲሁም ሌሎች አካላት ላደረጉት አስተዋጽኦ ፓርቲው ምስጋና አቅርቧል፡፡
ወንጀለኞችን አድኖ ለፍርድ ለማቅረብ ከሚደረገዉ ጥረት ጎን ለጎን በሕግ ማስከበር እርምጃው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና የፈራረሱ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ተጠግነው ለአገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ እንዲቀጥል ፓርቲው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በትግራይ ክልል የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፣ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ለማድረስና ሕብረተሰቡ ወደ መደበኛ የዕለት ተዕለት ህይወቱ እንዲመለስ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የፓርቲዉ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የኢትዮጵያ ህዝቦች የቻሉትን አስተዋጽዖ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ተገቢው እርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ኮሚቴው ከስምምነት ላይ መድረሱን ገልጿል፡፡
ይህንን ተግባር የሚፈጽሙ የጥፋት ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋልና እርምጃ ለመዉሰድ በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የብልጽግና አመራሮች በከፍተኛ ጽናትና ቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስቧል፡፡
ችግሮችን ለመፍታት የብልጽግና አመራሮችና አባላት ከሚለያዩ ጥቃቅን ጉዳዮች ወጥተው ከፍ ያለ ሀገራዊ እይታ በመያዝ ኢትዮጵያንና የሁሉንም ዜጎቿን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን በሚያደርግ መልኩ እንዲደጋገፉ፣እንዲረዳዱ፣ በአብሮነትና በትብብር መንፈስ እንዲሰሩ ጠይቋል፡፡
ኮሚቴው በ2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ ወደ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለምታደርገው ሽግግር ያለው ትርጉም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያምን እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና በሂደቱም ሆነ በዉጤቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡