አሜሪካ አጎአን አስመልክቶ ያሳለፈችውን ውሳኔ እንድትሰርዝ ኢትዮጵያ ጠየቀች
የአሜሪካ ውሳኔ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶስት የአፍሪካ ሀገራትን ከአጎአ እድል መሰረዟ ይታወሳል
አሜሪካ አጎአን አስመልክቶ ያሳለፈችውን ውሳኔ እንድትሰርዝ ኢትዮጵያ ጠየቀች።
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በትናትናው ዕለት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተጠቃሚ ከነበረችበት የአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አጎአ) ማስወጣታቸውን ለአገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከንግድ ችሮታው እንዲትወጣ ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ የጻፉት ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር ተያይዞ መሆኑንም ኋይት ሃውስ አስታውቋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ የአሜሪካ ውሳኔ በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ሊሆን አይችልም ብሏል።
የአሜሪካ ውሳኔ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው በሚሰሩ ከ200 ሺህ በላይ ወጣቶች እና ሴቶች ላይ የተቃጣ እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄዎችን እንደማያመጣ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።
ውሳኔው በዋነነት ከግጭቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸውን የማህበረሰብ አባላት እንደሚጎዳ የገለጸው ይህ መግለጫ በአጠቃላይ ከዚህ የውጪ ንግድ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው አንድ ሚሊዮን ዜጎችን እንደሚጎዳምም አስታውቋል።
የፌደራል መንግስት የሰሜንኢትዮጵያ ችግሮችን ለመፍታት የተቻለውን እያደረገ ቢሆንም አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች አገራት እና ተቋማት እየተደረገ ያለውን ጥረት ሊገነዘቡ እንዳልቻሉም የሚኒስቴሩ መግለጫ ያስረዳል።
በመሆኑም አገሪቱ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አጎአ) በማገድ ያስተላለፈችውን ውሳኔ እንድትቀለብስ በኢትዮጵያ ተጠይቃለች።
ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ጊኒ እና ማሊም ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አጉአ) እንዲወጡ በትናንቱ ደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
ሀገራቱ ይህ የተወሰነባቸው የአሜሪካን ፍላጎቶች ማሟላት ባለመቻላቸው መሆኑንም አሜሪካ ገልጻለች።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና ዋና የንግድ ተደራዳሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ “በእኛ እምነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአጎአ ተተቃሚ መሆን የምንችለው አሁን ነው” ብለው ነበር።
ከሰሞኑ አል ዐይን አማርኛ ኢትዮጵያ ይህንን የንግድ ችሮታ እንዳትጠቀም ቢወሰን የተዘጋጁ አማራጮች እንዳሉ አቶ ማሞን ጠይቆም ነበር።
ከፍተኛ አማካሪው አቶ ማሞ ለኢትዮጵያ አምራች ዘርፍ ሌላ አማራጭ የገበያ ዕድሎችም የማመቻቸት እንዲሁም የማምረቻ ወጭያቸው እንዲቀንስ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር።
አጎአ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገሮች የአሜሪካ መመንግስት የሚሰጠው ከቀረጥና ከኮታ ነጻ የንግድ ችሮታ ሲሆን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን የተፈረመ መሆኑ ይታወሳል።
20 ዓመት ያለፈው ይህ የንግድ ችሮታ እ.ኤ.አ 2025 እንደሚያበቃ እየተነገረ ቢሆንም የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላችም በሚል የንግድ ችሮታውን እንዳታገኝ የሚሰሩ አካላት እንዳሉ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።