ኢትዮጵያ ከአሜሪካው አጎአ እንድትወጣ “የሚጎተጉቱ”ት እነማን ናቸው?
“አንዳንድ የአሜሪካ መንግስት ኃላፊዎች” አጎአን የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ማስፈጸሚያ መሳሪያ ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን የጠ/ሚሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ገለጹ
“በእኛ እምነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአጎአ ተጠቃሚ መሆን የምንችለው አሁን ነው”- የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ
በአሜሪካ መንግስት ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ ሀገራት የሚሰጠው ከቀረጥና ከኮታ ነጻ የሆነው የንግድ ችሮታ (አጎአ) በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን የተፈረመ ነው። ይህ የንግድ ችሮታ 20 ዓመት አልፎታል።
ከአሜሪካ፤ ለአፍሪካ ሀገራት የሚሰጠው ይህ የንግድ ችሮታ በፈረንጆቹ 2025 እንደሚያበቃ እየተነገረ ነው። ይሁንና የአጎአ የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላችም በሚል የንግድ ችሮታውን እንዳታገኝ የሚሰሩ እንዳሉ መንግስት ገልጿል።
አል ዐይን አማርኛ የኢትዮጵያን ፤ የአሜሪካ የንግድ ችሮታን (አጎአ) ቆይታ በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና ዋና የንግድ ተደራዳሪ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አል ዐይን አማርኛ፡- የኢትዮጵያን የአጎአ ተጠቃሚነት በተመለከተ ከአሜሪካ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ላይ ነበራችሁ። በጉዳዩ ላይ ምን አዲስ ነገር አለ?
አቶ ማሞ፡- ኢትዮጵያ የአጎአ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላችም በሚል የንግድ ችሮታውን እንዳታገኝ ከብዙ አቅጣጫ የሚነሳ ጉዳይ አለ። አጎአ ከአሜሪካ፤ ለአፍሪካ ሀገራት የሚሰጥ የንግድ ችሮታ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረትም ተመሳሳይ ነገር አለው። የአጎአ ሕግ በፈረንጆቹ 2000 በፕሬዝዳንት ክሊንተን የተፈረመ ሲሆን፤ በየዓመቱ ሀገራት ቅድመ ሁኔታን አሟልተዋል ወይስ አላሟሉም የሚለው ይታያል። የእኛን በተመለከተ ኢትዮጵያ የአጎአ ተጠቃሚ መሆን የሚስችላት ቅደመ ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ አላሟላችም፤ ስለዚህ ተጠቃሚነቷ ጥያቄ ውስጥ ይገባል የሚል ከብዙ አቅጣጫ የሚነሳ ጉዳይ አለ። እሱን አስመልክቶ ነው እንግዲህ ከአሜሪካ መንግስት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያካሄድነው ። በእኛ እምነት ከመቸውም ጊዜ የተሻለ አጎአ ተጠቃሚ ልንሆንበት የምንችልበት ጊዜ አሁን ነው ብለን እናምናለን።
አልዐይን አማርኛ፡- አጎአን ለመጠቀም ጥያቄ የቀረበው ለምንድነው?
አቶ ማሞ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ተጠቃሚ መሆን የምንችልለው አሁን ነው የሚል ጽኑ እምነት አለን የሚል መከራከሪያ ይዘን ከአሜሪካ ጋር እየተነጋገርን ነው። የአጉዋን የንግድ ዕድል የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆን የሚፈልጉ ወገኖች አሉ፤ የአሜሪካ መንግስት ኃላፊዎችን፣ ኮንግረንሱን፣ ኢትዮጵያ ከአጎአ ተጠቃሚነት እንድትወጣ የሚጎተጉቱ፤ የሚወተውቱ ሰዎች አሉ፤ በአሜሪካም በሌላም ሀገር። በተጨማሪም አንዳንድ የአሜሪካ መንግስት ኃላፊዎች አጉዋን የፖለቲካ መሳሪያ ለማድረግ እና የፖለቲካ ፍላጎታውን ለማሟላት ኢትዮጵያ፤ የአሜሪካ መንግስት የሚለውን ካልፈጸመች ከአጎአ ተጠቃነት ልትወጣ ትችላለች የሚል ማስጠንቀቂያ የሚመስል ነገር በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር። ይህ የሚደበቅ ነገር አይደለም፤ አይደለም እኛ እነሱም የሚክዱት ነገር አይደለም።
አል ዐይን አማርኛ፡- መስፈርቶቹ ምንድናቸው?
አቶ ማሞ፡- ለንግድ እና ለኢንቨስትመንት ክፍት መሆን፤ የመንግስት አስተዳደሩ ብዙ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳተፍ ፤ የሕግ በላይነትን መቀበልና ማስከበር፤ በፋብሪካዎች የሚሰሩ ሰራተኞች መብታቸውን ማስከበር፤ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታውን ለአሜሪካ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስክበር የሚሉት ናቸው።
አሁን ያለው መንግስት ህወሃት መራሽ ከነበረው መንግስት ጋር ሲነጻጸር የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታውን ክፍት አድርጓል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተፈጻሚ እያደረግን ነው፤ በዛ መሰረት ከዚህ በፊት ዝግ የነበሩ ዘርፎችን ለኢንቨስትመንት ክፍት አድርገናል። የሰራተኞች መብቶች እናከብራለን፤ አሁን በተመሰረተው መንግስት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የፖለሪካ ስርዓት ነው ያለው። ህወሃት መራሽ በነበረው ስርዓት የዜጎችን መብቶች ሲይዙ የነበሩ ጨቋኝ የነበሩ ሕጎችን ያስተካከለው ይህ አስተዳደር ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ከባለፉት 20 ዓመታት በተለየ መልኩ የዜጎችን መብቶች በመጠበቅ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታውን ለኢንቨስተሮች ክፍት በማድረግ፣ ለግል ዘርፉ ተሳትፎ በቂና አስተማማኝ ቦታ በመስጠት እንዲሁም የሲቪል ማህበራት በፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን ተሳተፎ በማሳደግ ረገድ ከማናቸወም ጊዜ የተሻለ አውድ የተፈጠረበት ነው።
ኢትዮጵያ የአጎአ ተጠቃሚነቷ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል፤ ነገር ግን ይህንን ለማስቀረት የሚከራከሩ እንቅፋት ሊፈጥሩ የሚሞክሩ ሰዎች አሉ።
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ ከአጎአ እንድትወጣ የሚሰሩት እነማን ናቸው?
አቶ ማሞ፡- አንደኛ የሕወሃት ደጋፊ የሆኑ ሰዎች የሚከራከሩ ሰዎችን በመቅጠር በአሜሪካ ውስጥ ያሉ የኮንግረንስ ሰዎችን እንዲያሳምኑ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ መቸም በይፋ የሚታወቅ ነገር ነው። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሰዎች (አሜሪካ መንግስት ውስጥ ያሉ ሰዎችም) እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይን አስመከልክቶ ባለው ግጭት ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ሃሳቦችን፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች እንዲሟሉ በማድረግ አጎአን እንደ አንድ የውጭ ፖሊሲ መሳሪያ አድርጎ የማስቀረት ጉዳይ አለ።
በእኛ እምነት የፖለቲካ ሂደቱን በተመለከተ አጎአ ትክክለኛው መሳሪያ ነው ብለን አናምንም፤ ምክንያቱም አጎአ ከተነሳ የሚጎዱት በዋነኛነት በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰሩ ሰራተኞች ናቸው በተለይ ሴቶች ናቸው የሚጎዱት፡፡ ስለዚህ አንድ ሀገር የፖለቲካ መሳሪያውን ለማሳካት ሲባል ከጦርነቱ /ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች መጉዳት ትክክለኛ ነው ብለን አናምንም፡፡ ይህ እንዳይሆንም የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የዚህ የንግድ ችሮታ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው?
አቶ ማሞ፡- አጎአ ዕቃዎችን ወደ አሜሪካ የሚልኩ ሰዎች ፤ ዕቃዎችን በሚልኩበት ጊዜ የጉምሩክ ቀረጥ እንዳይከፍሉ ያደርጋል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ዋናው ዓላማ በአፍሪካ ውስጥ ያለው ኢኮኖሚ እርስ በእርሱ ይተሳሰራል የሚል እይታ አለ ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰቱም ይጨምራል ከሚል ዓላማ ነው፤ በጎ ዓላማ ያለው የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተቀየሰ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ይህን ተከትሎ አጎአን በተሻለ ለመጠቀም ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ በብዙ አካባቢዎች የተገነቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮፖች ቀላል ኢንስትሪ በመመስረት የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ ለመደገፍ ከዛም አልፎ ደግሞ የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ ኤክስፖርት መር እንዲሆን ለማስቻል የተደረገ ነው፡፡ ይህንን ዕቅድ በትልቁ የሚደግፈው የአጎአ ነው፡፡ ለምሳሌ ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚመረተው ምርት 90 በመቶ የሚሆነው የሚላከው ለአሜሪካ ነው፡፡ ስለዚህ አሜሪካ ውስጥ ያ ዕቃ በሚላክበት ጊዜ ቀረጥ አለመክፈሉ የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ ጠቀሜታው በጣም ጥሩ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- የንግድ ችሮታውን በኢትዮጵያ የሚያመርቱ አምራቾች ምን ያህል እየተጠቀሙበት ነው?
አቶ ማሞ፡- እንደሌሎች ሀገራት አጎአን ልንጠቀምበት የምንችለውን ያህል አልተጠቀምንበትም ፤ ለምሳሌ ኬንያን ብንወስድ ከኬንያ ወደ አሜሪካ ያለው ኤክስፖርት ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአሜሪካ ኤክስፖርት የምናደርገው ከ300 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም፡፡ ከዚህ ውስጥ እንዳውም ግማሹ ነው በአጉዋ የሚሄደው ፡፡ አንዳንዱም ለምሳሌ ቡናን ብንወስድ ቡና ላይ ቀረጥ ስለሌለ ድሮም ቢሆን የቡና ኤክስፖርት በአጎአ ተጠቃሚ ነው ብሎ ለመናገር ይቸግራል፡፡ በዋነኛነት አጎአ የሚመለከተው የአልባሳት ዘርፍን እና የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ነው ፡፡ ስለዚህ ልንጠቀም የምችለውን ያህል አልተጠቀምንም ፤ ከአጉዋ የምናገኘው ጠቀሜታ ግን ከአመት አመት እየጨመረ ነበር፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ ወረርሽኝን መቀዛቀዝ ተከትሎ ብዙ ፓርኮች ከፍተኛ የሆነ የገዥዎች ፍላጎት ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት አጎአ መነሳቱ ለእኛ ጉዳት ማድረሱ የማይቀር ነገር ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ የአጉዋ ተጠቃሚነትን ብታጣ ምን ይቀርባታል?
አቶ ማሞ፡- ምን ይቀርብናል የተለያዩ ነገሮች ናቸው ጉዳቱ ፤ አጎአ ከተነሳ የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ ተወዳዳሪ አያደርገውም ምክንያቱም ከዚህ በፊት ወደ አሜሪካ የአልባሳት ወይም የቆዳ ውጠየቶችን በምንልክበት ወቅት ወደ 16 /17 በመቶ የሚሆን ታክስ ይቀርልን ነበር፡፡ አሁን ያ ከተጨመረ የእኛን የጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ዘርፍ ተወዳዳሪ አያደርገውም ስለዚህ ኤክስፖርታችን በተወሰነ መልኩ መጎዳቱ አይቀርም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማንሳት የምፈልገው ይሄ ጉዳት በዋነኛነት ለአምራቾች እንጅ ለመንግስት አይደለም፤ ምክንያቱም ብዙ አምራቾች የሚያመጡትን ኤክስፖርት ራሳቸው ዕቃ ለመግዛት ነው የሚጠቀሙበት ፡፡ አሁንም ለአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ የምንናገረው አጎአን በመንካት የኢትዮጵያ መንግስትን ለመጉዳት ታስቦ ከሆነ ትክክል አይደለም፤ ምክንያቱም በዋነኝነት ውጤቱ አምራቾች ላይ ነው የሚለውን ነገር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አጎአ ከተነሳና አንዳንድ ኢንቨስተሮች ከወጡ የሚጎዳው እዛ አምራች ዘርፍ ላይ የተቀጠሩ ሰራተኞች በተለይ ሴቶች ሰራተኞች ናቸው፡፡ እዛ ውስጥ በቀጥታ የሚሰሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በአምራች ዘርፍ ጋር ተገናኝቶ በተዘዋዋሪ ጥቅም የሚያገኙ ሰዎችም ይጎዳሉ፡፡ ለምሳሌ ሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሰሩ ብቻ ሳይሆን ፤ ለፓርኩ የምግብ፤ የትራንስፖርት ፤ የቤት፣ የትምህርት አገልግሎቶችን የሚሰጡም ይጎዳሉ ማለት ነው፡፡
የሥራ ዕድልን በተመለከተ የሚመጣ ጉዳት አለ፡፡ በአሁኑ ሰዓት እኛ ከግብርና ዘርፍ ወደ አምራች ዘርፍ እየሄድን ስለሆነ እዛ ሽግግር ላይ የተወሰነ ጉዳት መኖሩ አይቀር ነው፡፡ቅድመ ሁኔታዎችን ስለምናሟላ በእኛ እምነት አጎአ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ተጠቃ መሆን አለባት፤ ለዘለዓለም ያለ አይደለም፡፡
አጎአ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ስምምነት አይደለም፡፡ ከአንድ ወገን የሚመጣ ስለሆነ ያ ወገን ሊያነሳው ይችላል፡፡ በእኛ እምነት ለማንሳት ግን መስፈርት ሊኖር ይገባል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ ይህንን የንግድ ችሮታ እንዳትጠቀም ቢወሰን የተዘጋጁ አማራጮች አሉ?
አቶ ማሞ፡- የተለያዩ ነገሮችን መስራት እንችላለን፤ ወደዛ ከሄድን አንደኛ ነገር ለእኛ አምራች ዘርፍ ሌላ አማራጭ የገበያ ዕድል ማመቻቸት አንደኛው ጉዳይ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የአምራቾችን የማምረቻ ወጭያቸው እንዲቀንስ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መስራት አለብን፤ ለምሳሌ የሎጄስቲክ ወጪ፤ የኃይል አቅርቦቱን በማስተካከል አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያን አምራች ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የማድረግ ስራ ሊሰራ ይችላል፡፡ እንግዲህ ይህንን ይህንን የምናደርገው ከአምራች ዘርፍ ውስጥ ከሚሳተፉ ሰዎች ጋር በጋራ በመገናኘት እና ውይይት በማድረግ ጉዳት እንዳይኖር ወይም ጉዳት ካለም ጉዳቱ የቀነሰ እንዲሆን መንግስት ተገቢውን ስራ ይሰራል።