ኢትዮጵያ ከአጎአ እድል በመታገዷ ምክንያት ከሀገር የተሰደደ ኩባንያ አለመኖሩ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ከለሙ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶች መካከል 84 በመቶው በባለሀብቶች ተይዘዋል ተብሏል
አሜሪካ ኢትዮጵያን ከንግድ ትስስር እድሉ የሰረዘችው ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር መሆኑን ገልጻ ነበር
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የንግድ ችሮታ (አግዋ) እድል በመታገዷ ምክንያት ከሀገር የተሰደደ ኩባንያ አለመኖሩን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በሰጡት መግለጫ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት 246 ሚሊየን ዶላር ገቢ እንዲያስገኙ ታቅዶ 196 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር አስገኝተዋል ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት፣ የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ፓርኮቹ በታቀደው ልክ ገቢ እንዳያስገኙ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ሰንዶካን አክለዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት በተለይም የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንደማይታወቅም አቶ ሰንዶካን አስታውቀዋል።
የህወሃት ታጣቂዎች በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ዝርፊያ እና ውድመት ማድረሳቸው እንዲሁም ሮኬት ወደ ባህርዳር መተኮሱ እና ወደ መሃል አገር ጥቃት መክፈቱ በባህር ዳር፣ ሰመራ እና ደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስጋት ምክንያት በፓርኮቹ የምርት መስተጓጎል አጋጥሞ እንደነበር ተገልጿል።
በአጠቃላይ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በተጠናቀቀው ዓመት ከ57 ሺህ በላይ ዜጎች የቀጥታ ስራ እድል መፈጠሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በሁሉም ኢንዱሰትሪ ፓርኮች ውስጥ 81 ሺህ ሰራተኞች በስራ ላይ እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመቀነስ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሀገር ውስጥ ምርቶችን በግብዓትነት እንዲጠቀሙ ለማድረግ በተሰራው ስራም 70 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ዋጋ ያላቸው የሀገር ውስጥ ምርቶች ለአምራቾች ቀርበዋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ካሏት 14 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 177 ሼዶች ሲኖሩ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ 15 ሼዶችን ሳይጨምር 136 ሼዶች ለአምራች ኩባንያዎች መተላለፋቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
ጦርነቱን ተከትሎ አሜሪካ ለአፍሪካዊያን የሰጠችው የአፍሪካ ዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ ወይም አግዋ መታገዷ ኢትዮጵያን እንደጎዳ የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው እገዳውን ተከትሎ ከሀገር የተሰደደ ኩባንያ አለመኖሩን አክለዋል።
“ የአግዋ እድል በመቅረቱ ምክንያት የማምረት አቅማቸውን እና የሰራተኞቻቸውን ቁጥር የቀነሱ አምራች ኩባንያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን በእግዱ ምክንያት ከኢትዮጵያ የተሰደደ አንድም ኩባንያ የለም” ሲሉ አቶ ሰንዶካን ተናግረዋል።
የታገደው የአግዋ እድል እንዲነሳ ከአሜሪካ ጋር ምክክሮች እና ውይይቶች ተካሂደዋል ያሉት አቶ ሰንዶካን በዚያው ልክ ግን የገበያ እድሎችን ለማስፋት ስራዎች መቀጠላቸውን ጠቁመዋል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያ ለዓመታት ተጠቃሚ ከነበረችበት አጎአ እድል ማስወጣታቸውን ለሀገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አሳውቀው ነበር።
ኢትዮጵያ ከንግድ ችሮታው እንድትወጣ ፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ የጻፉት በኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት በሰብዓዊ መብቶች ላይ ጥስት በመፈጸሙ ምክንያት መሆኑን ኋይት ሃውስ በወቅቱ ገልጾ ነበር።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጊኒ እና ማሊም ከእድሉ ታግደዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሜሪካ ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ አይሆንም ሲል በጽኑ መቃወሙ ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ ውሳኔው በኢንዱስትሪ ፖርኮች እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ላይ ተቀጥረው በሚሰሩ 200ሺ ወጣቶች እና ሴቶች ላይ የተቃጣ ሲል መግለጹ ይታወሳል።