የኢትዮጵያ ግብርና በሚወራው ልክ አልተሸጋገረም- የቀድሞ ጠ/ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ "ግብርና አሁን ፖለቲካ አይደለም" ብለዋል
የአፍሪካ የምግብ ሽልማት አዲስ ሊቀ-መንበሩን ሾመ
የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትርና የአፍሪካ የግብርና ድርጅት (አግራ) የቦርድ ሊቀ-መንበር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ግብርና በሚወራው ልክ እንዳልተሸጋገረ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና "ከሽንገላ ንግግር" አልፎ የሚያድገው መቼ ነው ተብሎ በአፍሪካ የምግብ ሽልማት መርሀ-ግብር ላይ ለተነሳላቸው ጥያቄ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር፤ ግብርና ማደጉን ነገር ግን አለመሸጋገሩን አንስተዋል።
- በጦርነቱ ምክንያት 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መታጣቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ
- ህወሓት ወደ ሰላም መምጣቱ የሚበረታታ መሆኑን የቀድሞው ጠ/ሚ አቶ ኃይለማርያም ገለጹ
የግብርና ሽግግር ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብን እንደሚጠይቅ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አንስተዋል። በዚህም መሰረት "ብዙ ይቀረናል" ያሉ ሲሆን ወጣቱን መሳብና ዘርፉን እንደ ንግድ ማየት አለብን ብለዋል።
በአጠቃላይ በአፍሪካ ግብርና መሄድ በነበረበት ልክ እንዳልሄደ ያነሱት ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ የግሉ ዘርፍ መሳተፍ እንዳለበት አስምረዋል።
በሀገራት ያሉ ተሞክሮዎችን በመከተል መስራት እንደሚቻል የኢትዮጵያን የስንዴ ልማት ለአብነት አንስተዋል። መልካም ጅምሮች እንዳሉ ሁሉ ብዙ እንቅፋቶች አሉ ያሉት ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ "ግብርና አሁን ፖለቲካ አይደለም" ብለዋል።
በአጭር ዓመታት እንደ ቻይና ግብርናን ለመለወጥ እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ችግሮች በየጊዜው መከሰት የትልቅ ፈተና መሆኑንም አንስተዋል።
ይህ ቢሆንም ግን የአፍሪካን ግብርና ለማዘመንና የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ አግራ በፈጠራና በሌሎች ዘርፎች ድጋፍ በማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
አግራ የተመሰረተበትን ኃላፊነት ለመወጣት አቅም እንዳለው የቦርድ ሊቀ-መንበሩ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አሳውቀዋል።
አግራ ለአፍሪካ የምግብ ዋስትናና የምጣኔ-ሀብት እድል በር ለከፈቱ ግለሰቦችና ተቋማት የሚሰጠው "የአፍሪካ የምግብ ሽልማት" አዲስ ሊቀ-መንበሩን ሾሟል።
የሽልማቱ ኮሚቴ የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኦሊሶግ ኦባሳንጆ ለቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ሚሪሾ ኪኪወቴ አስረክበዋል።
ሽልማቱ የአፍሪካን እርሻ ለሚያሸጋግሩ ግለሰቦችና ተቋማት 100 ሽህ ዶላር ይሸልማል።
ሽልማቱ ከተመሰረተበት ከፈረንጆቹ 2005 ጀምሮ የቀድሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ስራ አሰፈጻሚ ኢሌኒ ገ/መድህን (ዶ/ር) ጨምሮ ለ18 ተቀባዮች አድርሷል።