በጦርነቱ ምክንያት 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መታጣቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ
ከባለፈው ዓመት ያነሰ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ጅቡቲ ወደብ መድረሱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል
ሚኒስቴሩ 5 መቶ ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ሳይሸፈን መቅረቱን አስታውቋል
የግብርና ሚኒስቴር በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የምርት ቅነሳ እንዳጋጠመ አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለማረስና የእርሻ መሬቶቻቸውን በዘር ለመሸፈን ያልቻሉ አካባቢዎች መኖራቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህም የታቀደውን ያህል ምርት አልተሰበሰበም ያለው ሚኒስቴሩ ይገኝ የነበረ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መታጣቱን ገልጿል።
የሚኒስቴሩን እና የተጠሪ ተቋማቱን የ9 ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ/ም ያደመጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው፡፡
በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት 336 ነጥብ 60 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ተችሏል ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ለማምረት ይዘነው የነበረውን እቅድ 90 በመቶ አሳክተናል ሲሉ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ሆኖም በዘር በተሸፈነው የመሬት ስፋት ረገድ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ መኖሩንና 5 መቶ ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ሳይሸፈን መቅረቱን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ይገኝ የነበረ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መታጣቱን ነው አቶ ዑመር የገለጹት፡፡
ለእቅዱ አለመሳካት በጦርነቱ ምክንያት ማሳቸውን በዘር ያልሸፎኑ አካባቢዎች በመኖራቸው ነው ያሉም ሲሆን በሪፖርቱ የትግራይ ክልል አፈጻጸም አለመካተቱን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ሁኔታ ዘንድሮ እጅግ ፈታኝ እንደነበር ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከተገዛው 14 ነጥብ 51 ሚሊየን ኩንታል በ1 ነጥብ 61 ሚሊየን ኩንታል ያነሰ የአፈር ማዳበሪያ መገዛቱንም ነው የተናገሩት፡፡ ይህ በዋጋ መጨመር፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እና በአቅራቢዎች ፍላጎት ውስንነት ምክንያት የሆነ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ከተገዛው 12 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 83 በመቶ ያህሉን አጓጉዞ ጅቡቲ ወደብ ለማድረስ መቻሉንም አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት፤ በሪፖርቱ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡