ህወሓት ወደ ሰላም መምጣቱ የሚበረታታ መሆኑን የቀድሞው ጠ/ሚ አቶ ኃይለማርያም ገለጹ
ለአፍሪካ ሰላም የሚሰራው የጣና ፎረም ለኢትዮጵያ ሰላም ለምን ማምጣት አቃተው? ለሚለው ምላሽ ሰጥተዋል
በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ችግሮች በቶሎ ማይቋጩት የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ስላሉ ጭምር እንደሆነ አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል
የኢትዮጵያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚቀጥለው ሳምንት በባህር ዳር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የጣና ፎረም ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም ስለ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንደሚሰራ የሚገለጸው የጣና ፎረም ለምን በኢትዮጵያ ሰላም ላይ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም? በሚል አል ዐይን ለአቶ ኃይለማርያም ጥያቄ አንስቶላቸዋል።
እሳቸውም በምላሻቸው “የጣና ፎረም ስለ አፍሪካ የሰላም ችግሮች፣ መፍትሄዎች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ይሰራል፤ ተቋሙ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል በአፍሪካ እየተከሰቱ ላሉ የሰላም ችግሮች መነሻ ምክንያቶችን ማጥናት፣ የመፍትሄ ሀሳቦችን መጠቆም እና ወደ ፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የሰላም እና የልማት ስጋቶችን አስቀድሞ ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ ነው” ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ጥሩ ስራ ተሰርቷል የሚሉት አቶ ኃይለማርያም፤ የሰላም ችግር በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ አይደለም፣ በየትኛውም ሀገር የሰላም ችግር ሊከሰት ይችላል ፣ ዓለማችን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በየቦታው ብዙ የሰላም ችግሮችን እያስተናገደች ነው፣ ዋናው ነገር ከዚያ ለመውጣት ጥረቶች እና ሙከራዎች መኖራቸው ግን አስፈላጊ ነው ሲሉም አቶ ሀይለማርያም አክለዋል።
በአፍሪካ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የሰላም ችግሮች ምንጫቸው እንደ ጣና ፎረም አይነት ተቋሞች በሰላም ላይ ስላልሰሩ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ስላሉም ጭምር እንደሆነ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ከፌደራል መንግስት ጋር ወደ ጦርነት ያመራው ህወሓትም አሁን ላይ ወደ ሰላም መምጣቱ እና ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ፍላጎት ማሳየቱ መልካም እና የሚበረታታ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የጣና ፎረም ትኩረቱን በአፍሪካ ሰላም፣ አየር ንብረት ለውጥ እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ለማድረግ በሚል ነበር በ2002 ዓ.ም የተመሰረተው።
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተመሰረተው ይህ አህጉር በቀል ተቋም የፖሊሲ ግብዓት፣ የሰላም ችግሮችን በማጥናት እና የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመጠቆም በሚልም ነበር የተመሰረተው።
ተቋሙ ዓመታዊ ጉባኤውን የሀገራት መሪዎች፣ ምሁራን እና ሌሎች የአህጉር እና ዓለም አቀፍ የሲቪል ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ያካሂዳል፡፡
የዘንድሮውም ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በባህር ዳር እንደሚካሄድ የጣና ፎረም የቦርድ አባል እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በጉባኤው ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት በባህርዳር የሚካሄደው የጣና ፎረምም ዋነኛ ትኩረቱ የሰላም ጉዳይ እንደሚሆን ያነሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በመድረኩ ላይ የአፍሪካ ዋነኛ የሰላም ችግሮች ላይ ውይይት ተደርጎባቸው መፍትሄዎችን መጠቆም እንደሚሆንም አክለዋል።