የደ/ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና አቶ ኃይለማሪያም በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል
የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልዩ መልዕክተኛ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ወደ ደቡብ ሱዳን አቅንተው ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ እና በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የጋራ የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወን በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡
የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ቢትሪስ ካሚሳ ከውይይቱ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን ባደረጉት ንግግር፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ሁኔታ እና አሁን በሀገሪቱ መረጋጋት እየተፈጠረ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ቢትሪስ ካሚሳ እንዳሉት ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚከናወኑ የጋራ የልማት ፕሮጄክቶችን እንዲከታተሉ የተለያዩ ሚኒስትሮችን ሰይመዋል፡፡
ሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በማግኘቷ ፣ ጊዜው ፊቷን ወደ ልማት የምታዞርበትስለመሆኑ ሚስትሩ መናገራቸውንም የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው የአፍሪካን ቀንድ ማህበረሰብ ወደ አንድነት በማምጣት የኢኮኖሚ ፣ መሰረተ ልማት እና ንግድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ትስስርን ለመፍጠር ከአመራሩ ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ ፡፡
በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነትም ለፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት በደቡብ ሱዳን መረጋጋትን ለማምጣት የሰጡትን አመራርም አቶ ኃይለማርያም አድንቀዋል፡፡