ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት ተከሰሰች
ክሱን ያቀረበችው ግብጽ ስትሆን ኢትዮጵያ ሳታማክረኝ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ለአምስተኛ ጊዜ ውሃ ይዛለች በሚል ነው
ግብጽ ከኢትዮጵያ ውጪ ካሉ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ትብብሮችን ለማጠንከር መወሰኗን አስታውቃለች
ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት ተከሰሰች
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ተቃውሞ አለኝ የምትለው ግብጽ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ላይ ከሳለች፡፡
ግብጽ በዛሬው ዕለት ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸችው ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ለአምስተኛ ዓመት ውሃ ሙሌት አከናውናለች ይላል፡፡
በግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ስደተኞች እና ግብጻዊያን አርበኞች እንደተጻፈ የተገለጸው ይህ ደብዳቤ ኢትዮጵያ የግብጻዊያንን ጥቅም በሚጻረር መልኩ የውሃ ሙሌት እያካሄደች ነው ብሏል፡፡
በሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደል አቲ የተፈረመው ይህ የተመድ ደብዳቤ ኢትዮጵያ፣ግብጽ እና ሱዳን በፈረንጆቹ 2015 ላይ የተፈራረሙትን ስምምነት በመጣስ የግድቡ ውሃ ሙሌት በተናጠል ተከናውኗል፣ ይህም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅም የሚጎዳ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የግድቡን አምስተኛ ዓመት ሙሌት አስመልክቶ የተናገሩትን ንግግር የግብጽ መንገስት በፍጹም የማይቀበለው ነው የሚለው ይህ ለተመድ የተጻፈው ደብዳቤ የኢትዮጵያ አካሄድ ጎረቤት ሀገራትንን ጨምሮ የአካባቢውን ሀገራት ደህንነት የሚያናጋ ነውም ብሏል፡፡
ደብዳቤው አክሎም የኢትዮጵያ ግትርነት የሶስትዮሽ ሀገራት ውይይት እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑን፣ ከዚህ በፊት የተካሄዱ የሶስትዮሽ ውይይቶች ያለውጤት እንዲጠናቀቁ ኢትዮጵያ የይስሙላ ውይይት በማድረጓ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ የተናጠል አካሄድም የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ የሆኑት ግብጽ እና ሱዳንን ጥቅሞች ይጎዳል የሚለው ይህ የግብጽ ደብዳቤ በሱዳን እና ግብጽ እየደረሱ ያሉ የውሃ መጥለቅለቅ አደጋዎች የዚህ ውጤት ናቸውም ብሏል፡፡
በግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው የናይል ወንዝ የበላይ ኮሚቴ የሀገሪቱን ዜጎች ጥቅም ለማስከበር ከሌሎች የናይል ወንዝ ተፋሰስ አባል ሀገራት ጋር ትብብሮች አንዲደረጉ መወሰኑም በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል፤ መቼስ ይጠናቀቃል?
የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ከግብጽ ቀርቦለታል ስለተባለው አቤቱታ በይፋ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
ኢትዮጵያ በግብጽ ወደ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ስለተጻፈው ደብዳቤ እስካሁን በይፋ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን የህዳሴው ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ በተደጋጋሚ መናገሯ ይታወሳል፡፡
ግድቡ በተለይም በሱዳን እና ግብጽ ሲደርስ የቆየውን የውሃ መጥለቅለቅ እና ጎርፍ አደጋዎች እንደሚያስቀር በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ሲካሄዱ የነበሩ የሶስትዮሽ ውይይቶች ብዙ ልዩነቶችን መፍታት ያስቻሉ ቢሆንም የተፈለገው ስምምነት ልመጣው ግን በግብጽ ተለዋዋጭ አቋም እና ፍላጎት ምክንያት መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት ያወጣቸው መግለጫዎች ያስረዳሉ፡፡