ሶማሊያ የኢትዮጵያ አየርመንገድ በሀገሪቱ እንዳይበር ለማገድ ዛተች
የሀገሪቱ ሲቪል አቪየሺን ባለስልጣን አየርመንገዱ ከዚህ ቀደም ያቀረብኩትን “የሉአላዊነት ጉዳይ” ቅሬታ አልፈታም ብሏል
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የወደብ ኪራይ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ግንኙነት ሻክሯል
የሶማሊያ አቪየሽን ባለስልጣን የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ ሶማሊያ ከተሞች የሚያደርጋቸውን ሁሉንም በረራዎች ለማገድ ዝቷል።
ባለስልጣኑ ከዚህ ቀደም ያቀረብኩት “የሉአላዊነት ጉዳይ” ቅሬታ አልተፈጣም ያለ ሲሆን፥ ጉዳዩ እስከ ነገ ነሃሴ 17 2016 መፍትሄ ካልተሰጠው አየርመንገዱ ወደ ሶማሊያ ከተሞች እንዳይበር ለማገድ እንደሚገደድ ነው ያስታወቀው።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ እና ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር በታህሳስ ወር የተፈራረመችው የወደብ ኪራይ ስምምነት የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾን ግንኙነት ማሻከሩ ይታወሳል።
ሶማሊያ ሉአላዊነቴን ተዳፍሯል ያለችውን ስምምነት ተከትሎ ከወሰደቻቸው እርምጃዎች ባሻገር በማህበረሰብ አንቂዎቿ በኩል በኢትዮጵያ አየርመንገድ ላይ ተከፍቶ እንደነበር ይታወሳል።
የሶማሊያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በትናንትናው እለትም የአፍሪካ ቀዳሚው አየርመንገድ የሆነውና ወደ ሶማሊያ መዲናዋ ሞቃዲሾ እና የሶማሊላንድ ግዙፍ ከተማ ሃርጌሳ የሚበረው የኢትዮጵያ አየርመንገድ ላይ መግለጫ አውጥቷል።
የአቪየሽን ባለስልጣኑ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ ሶማሊያ ከተሞች ሲበር “የመዳረሻዎቹን ከተሞች አጭር መግለጫ አስወግዶ የአውሮፕላን ማረፊያዎቹን መለያ ኮድ ብቻ እየተጠቀመ ነው” ብሏል።
ችግሩ እንዲታረም ያቀረበው ቅሬታ አለመፈታቱን በመጥቀስም የአየርመንገዱ እርምጃ የሶማሊያ ሉአላዊነትን የሚጥስ መሆኑንም በመግለጫው ላይ አብራርቷል።
መግለጫው “ጉዳዩ እስከ ነሃሴ 17 2016 ካልተፈታ ከዚሁ ቀን ጀምሮ የሶማሊያ አቪየሽን ባለስልጣን ሁሉንም የኢትዮጵያ አየርመንገድ የሶማሊያ በረራዎች ለማገድ ይገደዳል” ይላል።
ከዚህ በኋላ መሰል ጥፋቶች ከተከሰቱም ያለምንም ማስጠንቀቂያ እገዳው እንደሚተላለፍም ነው ያሳሰበው።
የሶማሊያ አቪየሽን ባለስልጣን በኢትዮጵያ አየርመንገድ የሚበሩ የሀገሪቱ ዜጎች ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን እያቀረቡ መሆኑን ቢጠቅስም ዝርዝር ጉዳዮችን ግን አላነሳም።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ የሶማሊያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ስላቀረበው ቅሬታ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሻከረውን ግንኙነታቸውን ለማደስ ሁለት ጊዜ በአንካራ ተገናኝተዋል።
የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ባለፈው ወር የተካሄደው ሁለተኛው ዙር ያለስምምነት ቢጠናቀቅም “ተስፋ ሰጪ ለውጥ” ታይቶበታል ማለታቸው የሚታወስ ነው።