እርዳታ ወደ ትግራይ በመግባቱ ተቃውሞ ባይኖረውም ድጋፉ ፍትሀዊ እንዲሆን የአማራ ክልል ጠየቀ
በአማራ ክልል ሰባት ሚሊዮን ገደማ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል
ከኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም 800 ሺህ ደርሷል
በአማራ ክልል የረድዔት ድርጅቶች አድልዎ እየፈጸሙ መሆናቸው ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በየቦታው በተፈጠሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አምራች ዜጎች ለስደት እና እርዳታ ተዳርገዋል።
አማራ ክልል በዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑ ክልሎች ዋነኛው ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት እና በሌሎች ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም ከፍተኛው ሆኗል።
- በኢትዮጵያ ከእርዳታ ስርጭት ጋር በተያያዘ “ምንም አይነት መድልዎ” አይፈፀምም- የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን
- እርዳታ የጫኑ 47 ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ ጉዞ መጀመራቸው ተገለጸ
እንደ ተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ 28 ሚሊዮን ህዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያህሉ በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በክልሉ ውስጥ ላሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎችን ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል የተባለ ሲሆን 800 ሺህ ያህሉ ዜጎች ደግሞ ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ እንደሆኑ የአማራ ክልል መንግስት አስታውቋል።
የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና እንዳስታወቀው የሀገር ውስጥም ሆኑ ዓለም አቀፍ የረድዔት ተቋማት በአማራ ክልል ያሉ ድጋፍ ፈላጊዎችን የመርዳት ፍላጎት የላቸውም ብሏል።
የተቋሙ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ለአል ዐይን እንዳሉት “ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፎች በመሄዳቸው ተቃውሞ የለንም፣ ነገር ግን የሰብዓዊ ድጋፉ ፍትሃዊ መሆን አለበት” ብለዋል።
በአማራ ክልል ካሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ውስጥ 3 ነጥብ 5 ሚሊዩን ያህሉ በፌደራል መንግስት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ያሉት አቶ እያሱ፤ ቀሪው በክልሉ መንግስት ላይ ወድቋል፣ አሁን ላይ የክልሉ መንግስትም በቂ ሀብት የሌለው በመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ለደህንነታቸው ፈርተው ወደ አማራ ክልል የሚገቡ ተፈናቃይ ዜጎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ነው የሚሉት ሃላፊው በዋግ ሕምራ ዞን ስር ሲተዳደሩ የነበሩት አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች በህወሃት ታጣቂዎች ስር በመሆናቸው የተፈናቃዩ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንዲሄድ አድርጎታልም ብለዋል።
እንደ አቶ እያሱ ገለጻ ከጥቂት የረድዔት ድርጅቶች በስተቀር አብዛኞቹ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ሀገር በቀልም ሆኑ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ባላቸው የጸጥታ እና የፖለቲካ ፍላጎት ምክንያት እርዳታቸውን ከአማራ ክልል ይልቅ ወደ ትግራይ ክልል እየወሰዱ ናቸው።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ እና ከዋግ ሕምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ ተፈናቅለው ሰቆጣ ከተማ በተዘጋጀ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ አንድ እናት እንዳሉት “የሰላም ስምምነት ተፈረመ ሲሉን እኛም ሰላም እንሆናለን፣ ወደ ቤታችንም ተመልሰን መኖር እንጀምራለን ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” ሲሉ ነግረውናል።
አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች አሁንም በህወሃት ታጣቂዎች በመያዛቸው ምክንያት 80 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ሰቆጣ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀ ሶስት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በቂ እርዳተ በሌለበት ሁኔታ እየኖሩ መሆኑን ከክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ሰምተናል።