የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች እርዳታ ጭነው ትግራይ መግባታቸውን ህወሓት አስታወቀ
የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ኢሬፕቲ ደርሰዋል ያለው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከሰዓታት በኋላ መቀሌ እንደሚገቡ ገልጿል
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ 20 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ በመጓዝ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል
ሰብዓዊ እርዳታዎችን የጫኑ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ መግባት መጀመራቸውን ህወሓት አስታወቀ፡፡
የእርዳታ ተሽከርካሪዎቹ ትግራይ ክልል ገብተው ወደ መቀሌ መጓዝ መጀመራቸውን በትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጻቸው ያስታወቁት የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ 20 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ በመጓዝ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡
እርምጃውን በጥሩ ጎኑ ያነሱት አቶ ጌታቸው ዋናው ቁም ነገር ምን ያህል ተሽከርካሪዎች ተፈቀደላቸው ሳይሆን እርዳታው ሳይቆራረጥ እንዲደርስ ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት አለ ወይ? የሚለው ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
መንግስት፤ የትግራይ አማጺያን በጉልበት ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ጠየቀ
ሰብዓዊ እርዳታዎችን የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል መግባት መጀመራቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራምም አስታውቋል፡፡
ተሽከርካሪዎቹ ኢሬፕቲ ደርሰው ወደ ትግራይ ማቋረጥ መጀመራቸውን የገለጸው ፕሮግራሙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መቀሌ ይገባሉ ብሏል፡፡
ኢረፕቲ በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን ከሚገኙና ትግራይን ከሚያጎራብቱ አካባቢዎች አንዷ ናት፡፡
ከ500 ሜትሪክ ቶን በላይ የተመጣጠነ ምግብን በርሃብ አፋፍ ላይ ለሚገኙ የእርዳታው ፈላጊዎች አደርሳለሁም ነው ያለው፡፡
ከ1000 ሜትሪክ ቶን በላይ የተመጣጠነ ምግብን የጫኑ ሌሎች የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ዛሬ አርብ ከሰዓት መልስ በሰሜናዊ አፋር መድረሳቸውንም አስታውቋል፡፡
እርዳታው በዳሎል፣ በርሃሌ እና ኮነባ አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚደርስም፤ ተሽከርካሪዎቹ በሰላም እንዲያልፉ የአፋር ክልል መንግስትና ህዝብ ትልቅ ድጋፍ አድርገውልኛል ያለው ፕሮግራሙ ገልጿል፡፡
መንግስት የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ፍላጎቶቹን የሚያሟሉ እርዳታዎችን እንዲያገኝ በሚል ሙሉ በሙሉ ተኩስ ማቆሙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ህወሓት እርዳታዎች በተገቢው ሁኔታና ወቅት የሚደርሱ ከሆነ ለተኩስ አቁሙ ቁርጠኛ ነኝ ሲል እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ሆኖም እርዳታዎች በተባለው ልክ ወደ ትግራይ እየገቡ አይደለም የሚሉ ክሶችን ከሰሞኑ ሲያቀርብ ነበር፡፡
ህወሓት እርዳታዎችን በየብስ ወደ ትግራይ የማድረሱን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ ነው በሚል ክሱን ያስተባበለው መንግስት በበኩሉ በዓለም የምግብ ድርጅት እንዲያጓጓዝ የተፈቀደው በ43 መኪና የተጫነ የርዳታ እህል ወደ ትግራይ ማጓጓዝ አለመቻሉን ትናንት መግለጹ ይታወሳል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከሰዓታት በፊት ባወጣው መግለጫ ግን በዛሬዉ ዕለት በዓለም ምግብ ድርጅት አማካኝነት 21 ከባድ የጭነት መኪናዎች የእርዳታ እህል በመጫን በአፋር ክልል በአብዓላ መንገድ የሰብአዊ እርዳታ በየብስ ትራንስፖርት ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
መንግስት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱን በተሟላ ሁኔታ ለማስኬድ ከተባባሪና ባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ዛሬም ቁርጠኛ መሆኑን በድጋሚ ያሳውቃል ሲልም ነው አገልግሎቱ የገለጸው፡፡