እርዳታ የጫኑ 47 ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ ጉዞ መጀመራቸው ተገለጸ
የፌደራል መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ ግጭት ማቆሙን መግለጹ ይታወሳል
ሶስት ተሸከርካሪዎች ደግሞ ነዳጅ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል በመጓዝ ላይ መሆናቸው ተገልጿል
ምግብ የጫኑ 47 ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ ጉዞ መጀመራቸው ተገለጸ፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትዊተር ገጹ እንዳሳወቀው አልሚ ምግብ፣ አልባሳት፣ ነዳጅ እና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎችን የጫኑ 47 ተሸከርካሪዎች ወደ መቀሌ ጉዞ ጀምረዋል፡፡
ከ47ቱ ተሽከርካሪዎቹ በተጨማሪም ለመሰረታዊ አገልግሎቶች የሚውል ነዳጅ የጫኑ ሶስት ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ በመጓዝ ላይ መሆናቸውንም ነው ድርጅቱ የገለጸው፡፡
ዓለም ለዩክሬን የሰጠውን ያህል ትኩረት ለትግራይ እንዳልሰጠ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም መንግስት ሙሉ በሙሉ ተኩስ ማቆሙን ተከትሎ በቀን እርዳታ የጫኑ 100 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ስምምነት ላይ ቢደረስም ይህ እየሆነ አይደለም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን በትንሹ 2000 ገደማ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ሊደርሱ ይችሉ እንደነበር ቢገመትም "እስካሁን 20 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው ወደ ክልሉ የገቡት" ብለዋል፡፡
የቀድሞው የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል የመንግስትና የኤርትራ ወታደሮች ከበባ አሁንም ስለመቀጠሉ የተናገሩም ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ሰዎች በብሄራቸው ምክንያት ያለምንም ወንጀል በህይወት እያሉ ጭምር በእሳት እየተቃጠሉ እየሞቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ትግራይ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ገንዘብ እንዴት እያገኙ ነው?
ዶ/ር ቴድሮስ ራሳቸው ዓለም አቀፍ ተቋምን እየመሩ ገለልተኛ አይደሉም በሚል ይወቀሳሉ፡፡ ልክ እንደ ትግራይ ሁሉ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስላጋጠሙ ችግሮችና ህወሓት እንደፈጸማቸው ስለሚነገሩ ወንጀሎች በአደባባይ አይናገሩም በሚልም ስማቸው ይነሳል፡፡
ፖለቲካዊ ውግንና እንዳላቸው የገለጸችው ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የጤና ተቋማት ሲወድሙ ምንም ለማለት አለመቻላቸውን በማስታወስ ኢትዮጵያን ከተመለከቱ የትኞቹም ጉዳዮች ራሳቸውን እንዲያርቁ መጠየቋ ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ስልጣናቸውን አላግባብ እየተጠቀሙበት ነው ስትል ኤርትራ መክሰሷም አይዘነጋም።