በኢትዮጵያ ከእርዳታ ስርጭት ጋር በተያያዘ “ምንም አይነት መድልዎ” አይፈፀምም- የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን
በአማራና አፋር ክልሎች 25 ሺህ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች መሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ ስራ እየተካነወነ መሆኑንም ገልጿል
በሶስቱም ክልሎች ላሉ ተፈናቃዮች የሚደረገውን ድጋፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው መሆኑንም አስታውቋል
በትግራይ፣አማራ እና አፋር ክልሎች ላሉ ተፈናቃዮች የሚደረገውን ድጋፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን /የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ/ ገለጸ።
በኢትዮጵያ የኤጀንሲው ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን በማንሳት፤ ተመድ ተፈናቃዮቹን ለመደገፍ የተለያዩ ተግባራት እያከናወ ነው ብለዋል።
ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል በመዝለቁና የተፈናቃዮች ቁጥር እጅጉ መጨመሩ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ማድረጉንም ነው ቃል አቀባዩ የተናሩት።
ክሬቨንኮቪች “በሶስቱም ክልልሎች ያሉትን የተፈናቃዮች መጠን ከግምት በማስገባት የምናደርገው ድጋፍ በማሳደግ ላይ እንገኛለን፤ሰራተኞቻችን በሁሉም ቦታዎች እንዲደርሱ ከማድረግ አንጻርም የተቻለንን እያደረግን ነው” ብለዋል።
በአማራ እና አፋር ክልል ለሚገኙ 25 ሺህ ተፈናቃዮች እንደ ብርድ ልብስ፣ ሳሙና፣ የወጥ ቤት ቁሳቁሶች እና አጎበርን የመሰሳሉ መሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ የማዳረስ ስራ እየተሰራ መሆኑንም በአብነት አንስተዋል።
“የተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም በሁሉም ቦታዎች የምናደረገውን የድጋፍ ለማሳደግ ጥረት እያደረግን ነው” የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባለው ግጭት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ ለማዳረስ መቸገራቸው አስታውቀዋል።
“ሁኔታዎች ከተመቻቹ ተፈናቃዮችን ለመርዳት የሚያስችል በቂ የእርዳታ መጠን እንዳለም” ቃል አቀባዩ ኔቨን ክሬቨንኮቪች ተናግረዋል።
ከወራት በፊት “በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የነበሩና የተመድ ስደተኞች ኤጀንሲ መታወቂያ የያዙ ታጣቂዎች ተገኙ” የሚሉ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወሩና በተለያዩ የሚድያ አውታሮች ሲዘገቡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሚነሳውን ክስ በተመለከተ ቃል አቀባዩ ምላሽ ሰጥተውበታል።
ጉዳዩን የተለያዩ የመገነኛ ብዙሃን ሲዘግቡት በወቅቱ መመልከታቸው ያስታወሱት ቃል አቀባዩ ክሬቨንኮቪች፤ “ስደተኞቹን የተመለከቱ አዳዲስ መረጃዎች ሲገኙ፣ ከመጠለያ ጣቢያዎች ሲወጡም ሆነ መታወቂያ ካርዳቸው ሲጠፋ የመረጃ ቋታችን የምናዘምንበት መደበኛ የአሰራር ስርዓት አለን፤ ነገር ግን ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ሲወስኑ ስደተኛነታቸውን የሚያጡ ይሆናል” ብሏል።
ክሬቨንኮቪች ከወራት በፊት በጉዳዩ ላይ ለአል-ዐይን በሰጡት የኢ-ሜይል ምላሽ “በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ በስደተኞች የተደረገ እንቅስቃሴ አለመመልከታቸው” ገልጸው እንደነበርም የሚታወስ ነው።
አል-ዐይን ኒውስ ከእርዳታ ስርጭት ጋር በተያያዘ የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲን ጨምሮ በሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ላይ መንግስት የሚያነሳው “የፍትሃዊነት ጥያቄን” በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡበትም ቃል አቀባዩን ጠይቋል።
ቃል አቀባዩ በሰጡት ምላሽ “እንደ የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ በምንሰራባቸው ቦታዎቹ ሁሉ ያሉትን ስደተኞች እና ተፈናቃዮች በእኩል አይን ነው የምናየው” ሲሉ ተናግሯል።
ክሬቨንኮቪች አክለውም “ዩኤን.ኤች.ሲ.አር በትግራይ ክልል ብቻ አይደለም የሚሰራው፤ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ ስደተኞች የሚገኙበት የጋምቤላ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጽ/ቤት ከፍቶ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።
“አሁንም ቢሆን በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል የሚገኙ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች እየደገፍን ነው፤ ምንም መድልዎ የሚባል ነገር የለም” ሲሉም ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የጀመረውን የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት አሁን ላይ ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች ዘልቆ በአማራ ክልል ብቻ 1 ነጥብ 14 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከቀናት በፊት ለአል-ዐይን ኒውስ ማስታወቁ አይዘነጋም።