የአማራ ክልል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራቶቹ እንዲቆጠብ አስጠነቀቀ
የአማራ ክልል “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣው መግለጫ ጠብ አጫሪ ነው” ብሎታል
የአማራ ክልል “የትግራይጊዜያዊ አስተዳደር የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን እየገደለና እያሰቃየ ነው” ሲል ከሷል
የአማራ ክልል መንግስት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሀገሪቱን ና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራቶቹ እንዲቆጠብ አስጠነቀቀ።
የአማራ ክልል መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትናንትናው እለት ማለትም መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” ሲል ከሷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው፤ የአማራ ክልል መንግስት “የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ” በክልሉ ካርታ ላይ አስፍሯል፤ የትግራይ ክልል መሬቶች የሰፈሩበትን ካርታ በትምህርት ካሪኩለሙ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ ተረድቻለሁ” ማለቱ ይታወሳል።
የአማራ ክልል መንግስት ይህንን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ በተሳሳተ ካርታ ወደ አማራ ክልል ተካተዋል ያላቸውን አካባቢ ሕዝቦች ታሪካዊ እውነታን፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እና ነባራዊ ሐቅን የካደ፣ አሳሳችና የጠብ አጫሪነት ፍላጎትን የተሸከመ መግለጫ ነው” ብሎታል።
“የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአማራ ክልል የተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍ ውስጥ የተሳሳተ ካርታ ተሰርቷል ሲል ባወጣው መግለጫ ሊያመላክታቸው የተፈለጉት አካባቢዎች ካለፉት 30 ዓመታት በፊት ጀምሮ የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ሲያቀርቡባቸው በነበሩ ቦታዎች ናቸው” ብሏል የአማራ ክልል በመግለጫው።
“ህወሓት የሠሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን አሰቃቂ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎቹ ለዘመናት የታፈኑበት ሕዝብ ከማዕከላዊው መንግስት ጎን ተሰልፎ የበኩሉን አስተዋጽዖ ከማበርከቱ ባሻገር በሂደቱ ህወሓት በኃይል ተገፍፎባቸው የነበረውን የማንነትና ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት የተቀዳጁበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ብሏል የአማራ ክልል መንግስት።
የአማራ ክልል በመግለጫው “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከመማሪያ መጽሃፍ ካርታ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመፈጸም የማይመለስ መሆኑን የሚገልጽ የጠብ አጫሪ መግለጫ ማውጣቱ ካለፉት ድርብርብ ውድቀቶች ትምህርት አለመውሰድን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም” ብሏል።
የተፈጠሩ ችግሮችን በህግ አግባብ እንዲፈታ እተደረገ ያለውን ጥረት የአማራ ክልል መንግስት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ባለበት ሁኔታ በህዝብ መጎሳቆልና በወጣቶች እልቂት ትምህርት አለመወሰዱና የተለመደ ትንኮሳ በማድረግ ላይ መሆኑ እንዳሳዘነውም ገልጿል።
የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ ቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብ፣ ሀገራችንንና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራት እንዲቆጠብም የአማራ ክልል መንግስትአስጠንቅቋል።
እንዲሁም ጊዚያዊ አስተዳደሩ ከለመደው አጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር መክሯል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋት 16 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው፤ “የአማራ ክልል መንግስት “የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ” በክልሉ ካርታ ላይ አስፍሯል፤ የትግራይ ክልል መሬቶች የሰፈሩበትን ካርታ በትምህርት ካሪኩለሙ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ ተረድቻለሁ” ማለቱ ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያውጣውየተሳሳተ ካርታ ላይ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ በመግለጫው አስተጠንቅቆ ነበር።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን “ይህን ተከትሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የአማራ ክልል መሆኑን ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል።
የፕሪቶርያው ስምምነት በተሟላ መልኩ በመፈጸም እየተሰባለበት ወቅት የአማራ ክልል መንግስት የዚህ አይነት ተግባር መፈጸሙ “የሰላም ሂደቱን ለማደፍረስ ሆን ብሎ የሚፈጽመው ጥፋት መሆኑ” ሊሰመርበት ይገባል ብሏል።