የህዳሴ ግድብ ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ ገለጹ
የህዳሴ ግድብ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተጨማሪ 2800 ሜ.ኪ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ መጀመራውን አስታውቀዋል
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሕዳሴ ግድብ በበጀት ዓመቱ 17 በመቶ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨቱን አስታውቋል
የህዳሴ ግድብ ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት የኅዳሴ ግድብ 3ኛው እና 4ኛውን ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሌሎቹ ዩኒቶች በተቀመጠላቸው እቅድ መሰረት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለት ተርባይኖች በየካቲትእና ነሃሴ 2014 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው ይታወሳል።
የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ግድቡ ካሉት ተርባይኖች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ዩኒት 10 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ዩኒት 9 የሚባለው ሁለተኛው ተርባይን ደግሞ በዚያው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ኃይል የማመንጨት ጀምሯል።
ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ ከዚህ ቀደም ኃይል ማመንጨት የጀመሩ ሁለት ተርባይኖች በአጠቃላይ 540 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩ እንደሆነ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።
በትናንተሰናው እለት ሃይል ማመንጨት የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች ግድቡ የሚያመነጫን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በሁለት እጥፍ የሚያሳድገው ይሆናል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሰሞኑ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ ካመረተችው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ሕዳሴ ግድብ 17 በመቶ ድርሻ መሸፈኑን አስታውቋል።
በ2016 በጀት ዓመት 20 ሺህ 522 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት መቻሉን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ ከመነጨው ኃይል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የ34 በመቶ፣ ህዳሴ የ17 በመቶ እንዲሁም በለስ የ 9 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸውም ተጠቁሟል።
በተያያዘ ዜና የህዳሴ ግድብ በተጨማሪ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው በሰከንድ 2800 ሜኪ ውሃ ማፍሰስ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታውቀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍሰትን በመቆጣጠር፣ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በመቀነስ፣ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውሃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል ብለዋል።
“ይህ የተመዘነና የተመጣጠነ የውሃ ልቀት ግብርናን፣ የኃይል የማመንጨት ሥራን፣ በቀጠናው ያለ የሀብት አጠቃቀም ምጣኔን ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማል” ሲሉም አስታውቀዋል።