በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ላይ ጦርነት መቀስቀሱን ነዋሪዎች ገለጹ
ጦርነቱን የጀመሩት ሱዳን የሚገኙ የህወሃት ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል
በድንበር አካባቢ ባሉት በበረከት እና በዲማ በኩል አሁንም ተኩስ መኖሩ ተገልጿል
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ላይ በምትገኘው በረከት ከተማና አካባቢዋ በመንግስት ጦር እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት መቀስቀሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት በከፍተኛ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት መከፈቱንና ተኩስ መስማታቸውን ተናግረዋል።
- ሆነ ተብለው የተፈጸሙትን ሳይጨምር በጦርነቱ በአማራ እና አፋር ክልሎች 403 ንጹሀን መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ
- ከጦርነት በኋላ ህይወት በትግራይ ምን ይመስላል?
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጭ እንደሚሉት ከሁመራ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በረከት ተኩስ መሰማት ከጀመረ አራት ቀናት ተቆጥረዋል።
ጦርነቱን የተቀሰቀሰው በሱዳን ግዛት ውስጥ በሚገኙት የሃምዳይት እና የሉግዲ አካባቢዎች እንደሆነም የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ጦርነቱን ማን እንደጀመረው የጠየቅናቸው ነዋሪዎቹ፤ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ የህወሓት ኃይሎች ናቸው ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ፤ እንደሚሉት ከዚህ በፊት የፌዴራል መንግስት “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” ሲያውጅ ከሁመራ ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ የህወሓት ኃይሎች አሁን ላይ በሱዳን ግዛት ሆነው ጦርነት መክፈታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል።
ከበረከት በተጨማሪም በሁመራ ከተማ በሚገኘው ዲማ የፍተሻ ጣቢያ አካባቢም ጦርነት እንዳለ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ጦርነት እንደተቀሰቀሰበት የተገለጸው ዲማ የሚባለው የፍተሻ ጣቢያ በሁመራ በኩል ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚዋሰኑበት ድንበር ነው፡፡
ጦርነቱ በሱዳን ግዛት በኩል በመቅሰቀሱ ጉዳዩ የኢትዮጵያ እና ሱዳን እንደሆነ የሚገልጹ አካላት ያሉ ቢሆንም ይህ ግን ትክክል እንዳልሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በመሆኑም አሁን ያለው ጦርነት በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ጥምር ጦር እና ሱዳን በሚገኙ የህወሃት ታጣቂዎች መካከል መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ያለው ነገርም ሆነ ያወጣው መግለጫ የለም።
በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተጀመረው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት አንድ አመት የሞላው ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱ በሳላም እንዲቋጭ ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረ ከ8 ወራት በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ቢወጣም ህወሓት በአማራ አፋር ክልል ዘልቆ በመግባት መጠነ ሲፊ ጥቃት ማድረሱን መንግስት ይገልጻል፡፡
መንግስት ህወሓት ከያዛቸው ከአብዛኛው የአማራ እና አፋር ክልል ቦታዎች ማስለቀቁን ሲገልጽ ህወሓት ግን ለሰላም ሲባል መውጣቱን ገልጾ ነበር፡፡
በቅርቡ ብልጽግና ፓርቲ ባደረገው የመጀመሪያ ጉባዔ ከህወሃት ጋር ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት “የትኛውንም” የሰላም አማራጭ እንደሚጠቀም መግለጹ ይታወሳል።
የመንግስት ኩሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በማሰብ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውቋል፡፡