አሜሪካ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እያበረከተች ያለውን ጉልህ ሚና አደነቀች
የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለቱ አገራት 9ኛው የሁለትዮሽ የመከላከያ ኮሚቴ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሽንግተን ከተማ ተካሂዷል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም የምታበረክተው አስተዋጽኦ እና በመከላከያ ዘርፍ የምታካሄደውን ማሻሻያ አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ ባለፉት 18 ወራት በጸጥታው ዘርፍ ያላቸዉ ትብብር መጠናከር እንዳሳየ ኢትዮጵያና አሜሪካ ባወጡት የጋራ መግላጫ አስታውቀዋል፡፡
የሁለትዮሽ ግንኙነታቸዉ የበለጠ እንዲጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸዉንና ባለፉት 18 ወራት በጸጥታው ዘርፍ እያደገ የመጣው ትብብርም ለዚህ ማሳያ መሆኑን መግላጫዉን ይፋ ያደረገዉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል፡፡
የሁለትዮሽ የመከላከያ ኮሚቴ ስብሰባው ኢትዮጵያና አሜሪካ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በማበልጸግ በጸረ ሽብር፣ በደህንነት መረጃ እና ሌሎች የትብብር ዘርፎችን በመለየት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ከአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚ/ር አቶ ለማ መገርሳ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ቲቦር ናጅ ጋርም በአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በዋሽንግተን ዲሲ ተወያይተዋል፡፡
በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማልያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለቀጣናው ገንቢ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የልዑካን ቡድን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በአሜሪካ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ነው።