በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ሊደርስ የነበረውን የሳይበር ጥቃት መክሸፉ ተገለጸ
ዛሬ ህዳር 25/2012 ዓ.ም. በፋይናንስ ተቋማት ላይ ሊደርስ የነበረውን የሳይበር ጥቃት ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የፋይናንስ ተቋሞችን የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኢንተርኔት ኔትወርክ ለ 20 ደቂቃዎች ያክል ለማቋረጥ ተገድዶ እንደነበር የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተመሳሳይ ችግሮችን ለማክሸፍ ኤጀንሲው ከኢትዮ ቴልኮም ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በኤጀንሲ ውስጥ ኢትዮ ሰርት የሚባል የፋይናንስ ተቋማትን ለ24 ሰዓታት የሚከታተል እና አዲስ ጥቃቶች ሲቃጡ የመከላከል ተግባር የሚያከናውን ክፍል መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ክፍል አማካኝነት ጥቃቱ ሳይደርስ መከላከል እንደተቻለ ነው የተጠቆመው፡፡
ስራው ብዙ ጊዜ የተለመደውና የኔትወርክ ለውጥ የሚደረገው ብዙ ሰው ኢንተርኔት በማይጠቀምበት ሰአት ምሽት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ዛሬ ላይ የተፈጠረው አስቸኳይ ስለነበር ቀን ላይ እርምጃ ሊወሰድ ችሏል፡፡
ጥቃቱ ከየት እንደተሰነዘረ ዝርዝር ጉዳዮችን እየተመለከቱ እንደሆነም አቶ ወርቁ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ኢቢሲ