የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ ይፋ ተደረገ
በዋጋ ጭማሪው ቤንዚን 47 ነጥብ 83 በሊትር ፤ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 53 ነጥብ 10 በሊትር ሆኗል
አዲሱ የዋጋ ጭማሪ ከነገ ሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነው
ሲጠበቅ የነበረው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የዋጋ ማሻሻያው ከነገ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።
በተደረገው የዋጋ ጭማሪ መሰረትም፤
ቤንዚን --- 47 ነጥብ 83 በሊትር
ነጭ ናፍጣ --- 49 ነጥብ 02 በሊትር
ኬሮሲ --- 49 ነጥብ 02 በሊትር
ቀላል ጥቁር ናፍጣ --- 53 ነጥብ 10 በሊትር
ከባድ ጥቁር ናፍጣ --- 52 ነጥብ 37 በሊትር
የአውሮፕላን ነዳጅ --- 98 ነጥብ 83 በሊትር መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከላይ የተገለጸው የቤንዚን፣ የኬሮሲንና የነጭ ናፍጣ ዋጋ ላይ ለህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ወይም የታለመ ድጎማ ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች 15 በመቶ በመንግስት እንዲደጎምና ቀሪውን 10 በመቶ እንዲከፍሉ በማድረግ የድጎማ መጠኑን በቴሌ ብር ተመላሽ እንዲሆንላቸው ይደረጋል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ባስተላለፈው የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሰራር እና የመሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም ውሳኔ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የዋጋ ጭማሪው የተደረገውም የሚኒሰትሮች ሚክር ቤት በታህሳስ ወር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።