የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ነዳጅ ፍለጋ የገልፍ ሃገራትን መዞር ጀመሩ
ጉብኝቱን የሩሲያን የነዳጅ ጥገኝነት ለማስቀረት እንደሚያስችል እምነት ተጥሎበታል
ቦሪስ ጆንሰን በዩኤኢ እና በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ለማድረግ በማሰብ አቡ ዳቢ ገብተዋል
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ነዳጅ ፍለጋ የባህረ ሰላጤው ገልፍ ሃገራትን መዞር ጀመሩ፡፡
ጆንሰን ሳዑዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን (ዩኤኢ) ለመጎብኘት በማሰብ አቡዳቢ ገብተዋል፡፡
በነዳጅ ጉዳይ ወዳጅ የሆኑ የገልፍ ሃገራትን ለማግባባት በማሰብ ወደዚያው ማቅናታቸውም ተነግሯል፡፡
ጉዞው አውሮፓ በሩሲያ ነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማቅለል እንደሚያስችልም ነው የተነገረው፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ እንግሊዝን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እንዲሁም አሜሪካ እና የኔቶ አጋሮቿ ዐይነተ ብዙ ማዕቀቦችንና እገዳዎችን ጥለዋል፡፡ እገዳው በዋናነት ለሩሲያ ኢኮኖሚ የደም ስር ስለመሆኑ የሚነገርለትን ነዳጅን እና ሌሎች ንግድ ተኮር የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን ዒላማ ያደረገ ነው፡፡
ምዕራባውያን የሩሲያ ነዳጅ ላይ ማዕቀብ ከጣሉ በዓለም ገበያ ላይ ያልተጠበቀ አደጋ ያስከትላል ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች
ይህን ተከትሎ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ በዓለም ዓቀፍ ገበያ ከ130 ዶላር በላይ አሻቅቧል፡፡ አብዛኛውን የኃይል ፍላጎታቸውን ከሩሲያ በሚያስገቡት ነዳጅ ላይ ያደረጉ የአውሮፓ ሃገራትም ዋጋ ንረትን ጨምሮ ከባድ አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡
ጆንሰንም ነዳጅ አምራች የሆኑ የገልፍ ሃገራት ምርታቸውን እንዲያሳድጉ በማግባባት አደጋውን ለማቅለል ነው ቀደም ሲል ወደተጠቀሱት ሃገራት ያቀኑት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝት ለማስቀረትና ከሩሲያ ነዳጅ ማስገባቷን ለማቆም እቅድ ይዘዋል፡፡
ወደ ሳዑዲ አቅንተው ሞሃመድ ቢን ሳልማንን ከማግኘታቸው በፊት ዛሬ ረቡዕ በአቡ ዳቢ ከልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ዛይድ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ እና ዩኤኢ ብቻቸውን በቀን 13 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ያመርታሉ፡፡