ለመልሶ ማቋቋም የ5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተዘጋጀ
በጀቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን የተወካዮች ምክር ቤት ሲያጸድቀው ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል
ተጨማሪ በጀቱ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዳውን የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለመደጎም እንደሚውል መንግስት አስታወቋል
በጦርነትና በግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መዘጋጀቱን የገንዘብ ሚኒስተር አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራው የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፍነው አርብ በጉዳዩ ላይ ተወያይቷል፡፡
አቶ አህመድ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው የአምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ተጨማሪውን በጀት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳጸደቀው በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
መንግስት ከሚመድበው መነሻ በጀት በተጨማሪም ከልማት አጋሮች በተለይም ከአለም ባንክ ለመልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የመልሶ ማቋቋሙ መርሀ ግብሩ በመንግስት የሚመራ፣ የተቀናጀ፣ በየደረጃው በፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረግ፣ ተጠያቂነት ያለውና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ መሆኑንም ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡
በጦርነቱና በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅና በገንዘብ ለመተመን የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ ሀሳብ በገንዘብ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለመልሶ ማቋቋም ሴክሬታያት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቀርቧል፡፡
“ከሽንፈት አመድ ውስጥ ሳይሆን፤ የአሸናፊነትን አቧራ አራግፎ የሚነሳ የማገገሚያ ዕቅድ ያስፈልገናል”- ፕ/ር መንግስቱ
የኮሚቴ አባላትም የመልሶ ማቋቋም መርሀ ግብሩ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች በተጨማሪ በሌሎች ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉትንም እንዲያካትት፣ የሀብት አሰባሰብ ድግግሞሽ እንዲወገድና በአንድ ቋት እንዲሰባሰብ፣ ክልሎች ንቁ ተሳትፎ የሚደርጉቡት ምቹ ሁኔታ እንዲመቻች፣ ከሌሎች መሰል ብሄራዊ ኮሚቴዎች ጋር በቅንጅት እንዲሰራና የግሉን ዘርፍና ዲያስፖራውን እንዲያሳትፉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ የመልሶ ማቋቋም ሴክሬታሪያቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የትምህርት፣ የጤና፣ የፕላንና ልማት፣ የውሃና ኢነርጂ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ የስራና ክህሎት፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤት አመራሮች መገኘታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር በድረገጹ አስታውቋል፡፡