እስላሚክ ባንክ ምንድን ነው? ከንግድ ባንኮችስ በምን ይለያል?
አሁን ላይ በኢትዮጵያ 13 ባንኮች ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን በመስጠት ላይ ይገኛሉ
የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ከስምንት ዓመት በፊት አንስቶ በመሰጠት ላይ ይገኛል
እስላሚክ ባንክ በዓለማችን ካሉ የባንክ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ሲሆን አገልግሎቱ ተመሳሳይ ቢሆንም ስያሜው ግን ከሀገር ሀገር ይለያያል፡፡
ይህ የባንክ አገልግሎት በእንግሊዝ እስላሚክ ባንክ፣ ኢቲካል ባንክ የሚሉ ስያዌሞች ሲኖሩት በአሜሪካ ላሪባ ባንክ ሲባል በኢትዮጵያ ደግሞ ወለድ አልባ ባንክ ተብሎ እንዲጠራ የኢትዮጰያ ብሄራዊ ባንክ ደንግጓል፡፡
ከስምንት ዓመት በፊት አንስቶም በኢትዮጵያ ያሉ ሁለት የንግድ ባንኮች ወለድ አልባ ባንኮችን የጀመሩ ሲሆን አሁን ላይ 13 ባንኮች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለመሆኑ ወለድ አልባ ባንክ ማለት ምን ማለት ነው? ሲል አል ዐይን አማርኛ ከሌሎች የንግድ ባንኮች ስለሚለይበት አሰራሩና ስለ ትርፋማነቱ በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውን አቶ ሙባሪክ ሸሙሎን ጠይቋል፡፡
አቶ ሙባረክ በአሁኑ ወቅት ሂጀራ ባንክን በምክትል ስራ አስኪያጅነት በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
ወለድ አልባ ባንክ ከወለድ ነጻ ባንክ ይባል እንጂ ከወለድ ነጻ የሆነ አገልግሎት አይሰጥም ሲሉ የሚጀምሩት አቶ ሙባረክ ወለድ አልባ ባንክ ሸሪዓን መሰረት አድርጎ ለደንበኞች አገልግሎት በመስጠት ትርፍን ለማግኘት የሚሰራበት የባንክ ስርዓት መሆኑን ያነሳሉ፡፡
በሸሪዓ ህግ መሰረት በወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት የሚከለክላቸው የስራ ዘርፎች አሉ የሚሉት አቶ ሙባረክ ለአብነትም በአልኮል ንግድ፣ አሳማ እርባታ ፣የቁማር ንግድ፣ ሴተኛ አዳሪነት እና ከዚህ ጋር በተያያዙ የሆቴሎች አገልግሎት ዘርፎች እና ሌሎች ህብረተሰቡን ይጎዳሉ የተባሉ ሁሉ ክልክል መሆናቸውን በማሳያነት አስቀምጠዋል፡፡
ይሁንና ህብረተሰቡን እስከጠቀሙ ድረስ ግን በሌሎች የንግድ ስራዎችን በወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ወለድ አልባ ባንኮች ለደንበኞቻቸው አገልግሎት ለመስጠት ገንዘብ በቁጠባ፣ በጊዜ በተወሰነ የደንበኞች ቁጠባ ወለድ እና በሌሎች ደንበኞች እና ባንኩ በሚያደርጓቸው ስምምነቶች መሰረት ገቢ ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ለአብነትም ዋዲያ የሚባለው ወለድ አልባ ባንኮች ገቢ ያሚያገኙበት መንገድ ሲሆን ይህም ማለት የቀርድ ቼክ ሰዎች በብድር ባንኩ ጋር የሚያስቀምጡት ገንዘብ ሲሆን ደንበኞቹ ገንዘባቸውን በፈለጉት ጊዜ የመውሰድ መብትን ይሰጣቸዋል፡፡
ሁለተኛው የወለድ አልባ ባንኮች ገቢ ማግኛ መንገድ ሙዳራባ የሚሰኝ ሲሆን ደንበኞች ገንዘባቸውን ወደ ባንኩ እንዲያመጡ ካደረጉ በኋላ ባንኩ ያዋጣል ባለው የስራ ዘርፍ ያውለውና ትርፉን ደንበኛው ወይም ተቋሙ እና ባንኩ ቀድመው በተስማሙት መሰረት የሚገኝ ጥቅም ሲሆን ትርፍና ኪሳራን ባንኩ እና ደንበኞች የሚጋሩት አሰራር መሆኑን አቶ ሙባረክ ነግረውናል፡፡
ሌላኛው ወለድ አልባ ባንኮች ገቢ ያሚያገኙበት መንገድ ባይሰላ ስምምነት የሚባል ሲሆን ወደፊት ለሚመረት ምርት የሚደረግ ቅድሚያ ግዢ ለምሳሌ አዝርዕቶችን አሁን ባለው ዋጋ ከአልሚዎች በመግዛት ክፍያ ይፈጽማል ምርቱ ጊዜው ሲደርስ ከተሰበሰበ በኋላ ባንኩ ሸጦ የሚያገኘው ገቢ ነው ተብሏል፡፡
የወለድ አልባ ባንክ ደንበኞች የሚፈልጉትን ትላልቅ እቃዎች ግዢ በባንኩ በኩል ግዢ እንዲፈጸምላቸው የሚያደርጉት የሊዝ ግዢዎች ስምምነት ሲሆን ደንበኞች ከውጣ ውረድ ተገላግለው ባንኩ በራሱ መንገድ ግዢውን ፈጽሞ ከአገልግሎቱ የሚያገኘው ገቢ ሌላኛው የገቢ አይነት መሆኑንም ባለሙያው አክለዋል፡፡
ሌላኘው የወለድ አልባ ባንኮች ገቢ ማግኛ መንገድ ኢስቲስና ስምምነት የሚባል ሲሆን ይህ ደግሞ ግዙፍ የግንባታ ስራዎችን ከደንበኞች ሲቀርቡ ባንኩ ከደንበኞች ጋር በሚደረግ ስምምነት መሰረት አገልግሎቱን ሲፈጽም የሚገኝ ገቢ ነው ተብሏል፡፡
የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ሙስሊሞች ብቻ የሚጠቀሙት አይደለም የሚሉት አቶ ሙባረክ አገልግሎቱ ለሁሉም ህብረተሰብ ይሰጣልም ብለዋል፡፡
ወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ከሌሎች የንግድ ባንክ ተቋማት ልዩነታቸው የንግድ ባንኮች ብሄራዊ ባንክ በሚያወጣው አሰራር መሰረት የሚሰራ ሲሆን ወለድ አልባ ባንክ ግን ዋና መነሻው የሸሪዓ ህጉን መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀስመሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የወለድ አልባ ባንክ አሰራር በደንበኞች እና ባንኩ ስምምነት መሰረት ትርፍና ኪሳራን በመጋራት ከወለድ ዉጪ እና በአገልግሎት ገቢ ያገኛል፡፡
ለምሳሌም ሙሻረካ ስምምነት አንድ ደንበኛ ሀሳብ እና የተወሰነ ገንዘብ ይዞ ሲመጣ ስራውንም በጋራ ይመራሉ ባንኩ እና ደንበኛው ትርፉም ኪሳራውንም አስቀድመው በተስማሙት መሰረት ሲከፋፈሉ ሲሆን ሙዳራባህ ስምምነት አንድ ደንበኛ ጥሩ የቢዝነስ ሀሳብ ይዞ ሲመጣ ነገር ግን ግለሰቡ ለሀሳቡ ባንኩ ደግሞ ገንዘቡን ስላወጣ ትርፉን እና ኪሳራውን አስቀድመው በተስማሙበት መሰረት ሲከፋፈሉ ማለት ነው፡፡
በወለድ አልባ ባንክ አስራር መሰረት በአንድ የንግድ ስራ ውስጥ የተሰማራ ደንበኛ ከባንኩ አቅም ውጪ ያሉ ኪሳራዎችን ይጋራሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም ደንበኞች ከባንኩ ጋር የጀመሩት ስራ ኪሳራ ካስመዘገበ እና ቅጣቱን መክፈል ባይችል ባንኩ ተበዳሪን እንዳያስጨንቅ የሸሪዓ ህጉ አይፈቅድለትም፡፡ በዚህ ጊዜ ተበዳሪው አቅሙ በፈቀደ መጠን ራሱን ሊቀጣ የሚችል ሲሆን ይህን የቅጣት ገቢ ባንኩ እንደገቢ መውሰድ አይችልም ሲሉም ባለሙያው ገልቷል፡፡
በቅጣት የተገኙ ገቢዎች ለባንኩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እንደሚውሉ ባለሙያው አክለዋል፡፡