የደቡብ ሱዳን ሃይሎች ከሰሞኑ በካርቱም የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም ከሳምንት በኋላ ግን የተኩስ ድምጽ መሰማቱ ተገልጿል
በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት እና በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሪክ ማቻር መካከል ከሰሞኑ ስምምነት ከተደረገ በኋላ በሀገሪቱ ግጭት መቀስቀሱ ተገለጸ፡፡
የደቡብ ሱዳን ሃይሎች ከሰሞኑ በካርቱም የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም ከሳምንት በኋላ ግን ተኩስ ተሰምቷል ተብሏል፡፡
ግጭቱ የተነሳው በዩኒቲ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኩቺ ሜርሚር ካምፕ ውስጥ ነው ተብሏል፡፡ ለማቻር ታማኝ የሆኑ ሃይሎች በጦሩ በሚደገፉ ሚሊሻዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል መባሉ የግጭቱ መነሻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከማቻርም በሳልቫኪርም ወገን ያሉት ባለስልጣናት የሰጧቸው መግለጫዎች ግጭቱን ከማባባስ ይልቅ ስለሰላም መነጋገርን እደሚመርጡ አመላክተዋል ተብሏል፡፡የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ውጊያ እንዲቆምና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በሰላና በመከባበር እንዲኖሩ ያስፈልጋል ብለዋል ነው የተባለው፡፡
የደቡብ ሱዳን ጦር ምክትል አዛዥ ቱይ ቻኒ ሬይት ሁሉም ሃይሎች ግጭቶችን እንዲያቆሙና የተኩስ አቁሙን ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ ሳልቫኪር እና ማቻር ሥምምነቱን የተፈራረሙት በቀድሞ ሀገራቸውና በአሁኗ ጎረቤታቸው ሱዳን ነበር፡፡
ሁለቱ ወገኖች በወታደራዊ፣ በፖሊስ እና በብሔራዊ የጸጥታ ኃይሎች ውስጥ ከሚገኙት 60 ቁልፍ የአመራር ቦታዎች ውስጥ 40 የሚደርሱትን ለመከፋፈል የሚደነግገውን የሥምምነት ተፈራርመው ነበር፡፡ በዚሁ የስምምነት ወቅትም፤ የሳልቫኪር ጸጥታ አማካሪ ቱት ጋትሉክ `` እኛ ደቡብ ሱዳናውያን ሰላም እንደምንፈልግ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል፤ ሁላችንም ለሠላም እንስራ ብለው ነበር፡፡