ቡርሃን ከሱዳን ሊያባርሯቸው እንደሚችሉ ከዛቱባቸው የተመድ ተወካይ ጋር ተወያዩ
ሱዳን ተወካዩ ከተልዕኳቸው ውጭ ጣልቃ እየገቡ ነው በሚል ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቋ ይታወሳል
ውይይቱ ተወካዩ ከሰሞኑ ለጸጥታው ምክር ቤት ከሰጡት ማብራሪያ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል
የሱዳን ጦር መሪ ጄ/ል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ከሱዳን ሊያባርሯቸው እንደሚችሉ ከዛቱባቸው የተመድ ተወካይ ጋር ተወያዩ፡፡
ቡርሃን በራሳቸው በቮከር ፔርቴዝ ጥያቄ ነው አግኝተው ያወያዩዋቸው፡፡
ቮከር ፔርቴዝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሱዳን ሽግግር የድጋፍ ተልዕኮ መሪ እንዲሁም በሱዳን የተመድ ዋና ጸሃፊ የአንቶኒዮ ጉቴሬዝ ልዩ መልዕክተኛ ናቸው፡፡
የሱዳንን የለውጥ ሂደት ሂደት ይደግፋሉ በሚልም ነው የተሰየሙት፡፡ የሱዳን ፖለቲካ ኃይሎችን በማስተባበር ወደ መግባባት ሊያመጣቸው የሚችልን መደላድል እንደሚፈጥሩም ነው የሚታሰበው፡፡
ሆኖም ከሰሞኑ ሱዳን ከገጠማት ፖለቲካዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት የሰጡት ማብራሪያ ወትሮም ቢሆን በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገባ ነው በሚል ይከሱ የነበሩትን የሃገሪቱን ባለስልጣናት አስቆጥቷል።
የሱዳንን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት አል ቡርሃንም ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጭ እያደረጉት ያለው ተግባር ከሀገሪቱ ሊያስባርራቸው የሚችል ነው በሚል በልዩ መልዕክተኛው ላይ ሲዝቱ እንደነበርም ነው የተነገረው፡፡
ተመድም ሆነ የአፍሪካ ህብረት ውይይቶችን ከማመቻቸት በዘለለ በሱዳናውያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሚል ሲያሳስቡ የነበሩት ቡርሃን የሃገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተከፈተ ሲናገሩም ነበረ፡፡
ውይይቱ ፔርቴዝ ለጸጥታው ምክር ቤት ከሰጡት ማብራሪያ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ነው የሃገሪቱ ዜና አገልግሎት የዘገበው፡፡
ማብራሪያው የተሟላ አይደለም በሚል ልዩ መልዕክተኛውን የወቀሱት ቡርሃን ተልዕኮው ጦሩን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ አካላት በሚዛናዊነት ሊመለከት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ማብራሪያው ካርቱም የሚገኘው ጽህፈት ቤታቸው ካሰባሰባቸው መረጃዎች በመነሳት መሰጠቱን የገለጹት ፔርቴዝ በበኩላቸው ለምክር ቤቱ ባስገቡት ሪፖርት ተዛብተው የተካተቱ መረጃዎች ካሉ ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄ/ል መሀመድ ሃምዳን ደጋሎ ተመድ በሱዳን ጉዳይ“አመቻች እንጂ አስታራቂ" አይደለም በሚል ልዩ መልዕክተኛው በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ ማሳሰባቸውም የሚታወስ ነው፡፡