ሉሲ (ድንቅነሽ)ን ጨምሮ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ልዩ ልዩ የሀገሪቱ መገለጫዎች ይቀርባሉ
በኮቪድ 19 ሳቢያ የተራዘመው የዱባይ 2020 ኤክስፖ የመከፈቻ ስነ ስርዓት ትናንት ምሽት የተካሄደ ሲሆን፤ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 6 ወራት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ኢትዮጵያ በዱባይ ኤክስፖ የኢንቨስትመንት አማራጮቿን፣ ንግድና ቱሪዝም እድሎቿን ለማስተዋወቅ ስትሰራ የቆየች ሲሆን፤ ሀገሪቱን ለማስተዋወቅ ይበጁኛል ያለቻውን በሙሉ ወደ ስፍራው ይዛ ተጉዛለች።
- በዱባይ ኤክስፖ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት፣ንግድና ቱሪዝም ለማስተዋወቅ እየተሰራ ነው-ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
- አል ዐይን ኒውስ ለዱባይ ኤክስፖ 2020 ሙሉ ሽፋን ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል
በኤክስፖው ላይ ኢትዮጵያን የሚገልጹ ሙዚቃዎች፤ ባህሎች እና ሀገሪቱን የሚያስታውሱ የተለያዩ ቀኖች ተሰይመው የሚከበሩ መሆኑን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም መግለጹም ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በዱባይ 2020 ኤክስፖ ምን ይዛ ቀርባለች…?
ሉሲ (ድንቅነሽ)
ሉሲ ድንቅነሽ በኤክስፖ 2020 ዱባይ ላይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ቀደም ብላ ዱባይ የገባች ሲሆን፤ በኤክስፖው ሉሲ ለ6 ወራት ለጎብኚዎች ለእይታ ትቀርባለች። ሉሲም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለም ማህበረሰብ በኤክስፓው ለእይታ ትቀርባለች።
ከሉሲ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ታሪክ እና ባህል የሚያሳዩ የተለያዩ ቁሳቁሶች በተንቀሳቃሽ ምስል ተደግፈው ለጎብኚዎች የሚቀርቡ ይሆናል።
ጤፍ
በኤክስፖ 2020 ዱባይ ላይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ከሚቀርቡ ምርቶች ውስጥ ጤፍ ሌላኛው ሲሆን፤ ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚመረተው ጤፍ፤ ምን ይመስላል፣ በምን መልኩ ይመረታል፣ በምን አይነት ሂደት ውስጥ ያልፋል የሚለው በተንቀሳቃሽ ምስል ተደግፎ የሚቀርብ ይሆናል።
ቡና
የኢትዮጵያ ቡና በኤክስፖው ላይ ከሚቀርቡት ውስጥ አንዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የቡና ምርት ታሪክ፣ የቡና አመራረት ሂደት እና የቡና ፍሬ ለእይታ የሚቀርብ ይሆናል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የቡና ባህላዊ የቡና ማፍላት ስነ ስርዓት በኤክስፖው ላይ ለጎብኚዎች የሚቀርብ ይሆናል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የቡና ቀን፣ የአትሌቶች ቀን፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቀን፣ የቁንጅና ውድድር፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ቀን፣ የኢትዮጵያ ምግቦች የሚቀመሱበት የኢትዮጵያ ልዩ ጣእም ቀን፣ የኢንቨስትመንት ፎረም እና የኤክስፖርት ምርቶች ሳምንት በሚል የተለያዩ ሁነቶች በኤክስፖው ላይ የሚዘጋጁ ይሆናል።
የዱባይ ኤክስፖ 2020 ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 192 ሀገራት እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከ25 ሚልየን በላይ ጎብኚዎች እንደሚጎበኙበትም ይጠበቃል።
የዱባይ 2020 ኤክስፖ ከጥቅምት እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም ለስድስት ወራት እንደሚካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ መራዘሙም ይታወሳል።
በአረብ ሀገራት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ለተነገረለት የዱባይ ኤክስፖ 2020 ከ10 ዓመት በላይ የፈጀ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።