በፓኪስታን የኢምራን ካን ደጋፊዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው የጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ ተቃውሞውን "ሰላማዊ ነገር የሌለው ጽንፈኝነት" ነው ሲሉ ኮንነውታል
የፓኪስታን ጦር የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ወደሚገኝበት አካባቢ ሰራዊቱን ማሰማራቱን አስታውቋል
በፓኪስታን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን እንዲለቀቁ አደባባይ የወጡ ደጋፊዎቻቸው ከየጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩት የካን ደጋፊዎች በሀገሪቱ ፓርላማ አቅራቢያ ያካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ ነውጠኛ ነበር ያለው የፓኪስታን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አራት የፈጥኖ ደራሽ ሃይል አባላት መገደላቸውን ገልጿል።
ተቃውሞው ወደ ሁከት እያመራ በመሆኑም በመዲናዋ ኢስላማባድ የስአት እላፊ እንደሚጣልም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
የፓኪስታን ጦር የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች እና የመንግስት ተቋማት በሚገኙበትና "ቀይ ክልል" በሚባለው አካባቢ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ለመጠበቅ ሰራዊቱን ማሰማራቱም ተጠቁሟል።
የጸጥታ ሃይሎች በተሽከርካሪዎች ላይ በመሆን ተቃውሟቸውን ሲገልጹ በነበሩት የካን ደጋፊዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ሰልፉን ለመበተን ሲጥሩ መታየታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ ተቃውሞውን "ጽንፈኝነት" ነው ሲሉ ኮንነውታል።
ደማ የፈሰሰበት ተቃውሞ "መጥፎ የፖለቲካ አላማ ለማሳካት" ያለመ መሆኑን በመጥቀስም ድርጊቱን ተቃውመውታል።
የካን ፓኪስታን ተህረክ ኢ ኢንሳፍ (ፒቲአይ) ፓርቲ በበኩሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከእስር እስከሚለቀቁ ድረስ ለተቃውሞ የወጡት ሰልፈኞች ወደቤታቸው እንደማይመለሱ ገልጿል።
የብረት ዘንድ፣ ወንጭፍ እና ዱላ የያዙት ተቃዋሚዎች ዛፎችን ሲያቀጣጥሉ መታየታቸውን ሬውተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የካን ደጋፊዎች በኮንቴነሮች የተዘጉ መንገዶችን ጥሰው በማለፍ ፥ካን ካልተፈቱ አንነሳም" የሚለውን ተቃውሞ ለመቀላቀል እየሞከሩ ነው መባሉም የኢስላማባድን ውጥረት አባብሶታል።
የመንግስት ተሽከርካሪዎችን በመዝረፍና የፖሊስ ቢሮዎችን በማቃጠል ላይ ናቸው የሚሉ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።
የፓኪስታን መንግስት ተቃውሞዎቹ እንዲበርዱ ከኢምራን ካን አማካሪዎች ጋር ቢመክርም ስኬታማ እንዳልነበር የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ካዋጃ ሙሀመድ አሲፍ ተናግረዋል።
ካን በ2022 ከስልጣናቸው ተነስተው ከሙስና እና ግጭት ከመቀስቀስ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ባለፈው አመት ነሃሴ ወር ላይ መታሰራቸው ይታወሳል።