ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን በ2008 ባልቃወም ኖሮ ጦርነቱ ቀድሞ ይጀመር ነበር - ሜርክል
ጀርመንን ለ16 አመት የመሩት አንጌላ ሜርክል ኬቭ ኔቶን የመቀላቀል ሂደት አስቀድማ ብትጀምር ከአሁኑ የከፋ ችግር ውስጥ ትወድቅ ነበር ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ግን የሜርክል ተቃውሞ ሩሲያን ያጠናከረ "የተሳሳተ ስሌት" ነበር ብለዋል
የቀድሞ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ዩክሬን የሰሜን ቃልኪዳን ጦር ድርጅትን (ኔቶ) እንዳትቀላቀል መቃወማቸው ትክክል እንደነበር ተናገሩ።
በአውሮፓ ፈርጣማ ኢኮኖሚ የገነባችውን ሀገር ለ16 አመት የመሩት ሜርክል "ዩክሬን ኔቶን የመቀላቀል ሂደት በ2008 ብትጀምር ጦርነቱ አስቀድሞ ይጀመር ነበር" ብለዋል።
ሜርክል ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኬቭ በየካቲት 2022 እንዳላት አይነት ወታደራዊ አቅም ባልፈጠረችበት ሁኔታ የጦር ቃልኪዳን ድርጅቱን መቀላቀሏ ከአሁኑ የከፋ ችግር ውስጥ ይከታት እንደነበር ነው ያብራሩት።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የዩክሬንን ኔቶን የመቀላቀል ጥረት እንደቀላል ነገር እንደማይመለከቱት ተረድቼ ነበር ይላሉ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን የቀድሞ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን አስተያየት አይቀበሉትም።
ሜርክል እና የወቅቱ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ኬቭ ኔቶን እንዳትቀላቀል ማገዳቸው ሩሲያን ያጠናከረ "የተሳሳተ ስሌት" ነው ብለውታል።
ከስልጣናቸው ከለቀቁ ከሶስት አመት በኋላ ቃለመጠይቅ የሰጡት ሜርክል ለሁለት አስርት አመታት የሚያውቋቸው ፑቲን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሰሙት ያለው የኒዩክሌር ዛቻ ስጋት ፈጥሮባቸዋል።
"የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን፤ ቻይናም ይህንኑ ጉዳይ እያነሳች ነው፤ ሩሲያ እና አሜሪካ በኒዩክሌር አቅም ቀዳሚዎቹ ቢሆኑም በፍርሃት ተሸብበን ዝም ማለት የለብንም" ሲሉም ነው የተናገሩት።
ሜርክል ከሩሲያ ጋር ሰላማዊ ትብብር ለመመስረትና የዩክሬን ጦርነት እንዳይጀመር በ16 አመት የስልጣን ቆይታቸው የሚችሉትን ሁሉ ስለማድረጋቸውም አብራርተዋል። በርግጥ ፑቲን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የሚል ስያሜ የሰጡትን የዩክሬን ጦርነት የጀመሩት ሜርክል ስልጣን ከለቀቁ ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር።
የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ "የአውሮፓ ህብረት መሪ" የሚሏቸው አንጌላ ሜርክል ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የነበራቸው ወዳጅነት በአውሮፓውያኑ ዘንድ ያስወቅሳቸው ነበር።
በሜርክል የስልጣን ዘመን ሃይል የተጠሙ የሀገሪቱ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች የሞስኮ ጥገኛ ነበሩ። በርሊን ከሩሲያ ጋር የሚያገናኙ ሁለት የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያዎችን መገንባቷም ይታወሳል።
የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመሩ የጀርመንን የሃይል ፍላጎት ከመመለስ ባሻገር ከሞስኮ ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን ለመመስረት ወሳኝ ድርሻ እንደነበረው ሜርክል አውስተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ግን ክሬምሊን የሞስኮ ርካሽ ጋዝን የጂኦፖለቲካል ጥቅም ማስከበሪያ አድርጎት ነበር ብለዋል።
ምዕራባውያን የኬቭ አጋሮች ጀርመን ከሩሲያ የምትገዛው የተፈጥሮ ጋዝ ሞስኮ በዩክሬን የጀመረችውን ጥቃት እንድታጠናክር ያደርጋል በሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውና ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
በዚህም የጀርመን ኢንዱስትሪዎች የተፈጥሮ ጋዝ ከሌሎች ሀገራት በውድ ዋጋ ለመግዛት እየተገደዱ ይገኛሉ ተብሏል።