ከኳታር ህዝብ 1 ነጥብ 2 ከመቶው ሮናልዶን ለማየት ስታዲየም ገብቷል
ፖርቹጋላዊው ኮከብ አልናስር የኳታሩን አል ጋራፋ 3 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ጎሎች አስቆጥሯል
የሳኡዲው ክለብ በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ውስጥ ለመግባት ተቃርቧል
ፖርቹጋላዊው የአለማችን የእግርኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በኳታር ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
ቡድኑ የሳኡዲው አል ናስር በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ከኳታሩ አል ጋራፋ ጋር ትናንት ተጫውቷል።
ጨዋታው የተካሄደው ከዶሃ በ50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አል ባይት ስታዲየም ነው።
ይሁን እንጂ 37 ሺህ የሮናልዶ ወዳጆችና የአል ጋፋር ደጋፊዎች ስታዲየሙን ሞልተውታል።
በስታዲየም የተገኙት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች፣ ታዳጊዎች እና እግርኳስ አፍቃሪዎች ቁጥር ከባህረሰላጤዋ ሀገር ጠቅላላ ህዝብ 1 ነጥብ 2 ከመቶውን ይሸፍናሉ ተብሏል።
አብዛኞቹ ተመልካቾች የ21ኛው ክፍለዘመን የእግርኳስ ፈርጡን ለመመልከት የገቡ መሆናቸውን የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
አልናስር 3 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ሮናልዶ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል። በሳኡዲ ፕሮ ሊግ የሚጫወተው ቡድን በቀጣይ ከሚያደርጋቸው ሶስት የምድብ ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ከሰበሰበ ወደ ጥሎ ማለፉ ይቀላቀላል።
ሮናልዶ ከአል ባይት ስታዲየሙ ድል በኋላ በሰጠው አስተያየት "ታዳጊ አድናቂዎቼ በእግርኳስ መድረክ አሁንም መጫወቴን እንድቀጥል ትልቅ መነሳሳት ይፈጥሩልኛል" ብሏል።
የካቲት 5 2025 ላይ 40ኛ አመት ልደቱን የሚያከብረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የእግርኳስ ዘመኑ እያለቀ ነው የሚሉ አስተያየቶች በተደጋጋሚ ቢሰጡም ጎሎችን እያስቆጠረ አሁንም ተጽዕኖ ፈጣሪነቱን እያሳየ ይገኛል።
ሮናልዶ ከ2022ቱ የአለም ዋንጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ ኳታር ያቀናው። ሮናልዶ ሀገሩን በአለም ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ ወዳደረሰባት ኳታር ተመልሶ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሩን ተከትሎ ያገባቸውን ጎሎች ቁጥር 915 አድርሷል።
"ወደ ኳታር መመለስ ጥሩ ስሜት አለው፤ በተለይ ታዳጊዎች ለእኔ እና ለእግርኳስ ያላቸውን ፍቅር ማየት ደስ ያሰኛል፤ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሬም ወደ ሳኡዲ በደስታ እንድመለስ ያደርገኛል" ሲል ለኳታር መገናኛ ብዙሃን አስተያየቱን ሰጥቷል።
ትናንት የኳታሩን አል ጋራፋ ያሸነፈው አል ናስር ከምድብ ሁለት በ13 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
24 ቡድኖች በሁለቱ ምድቦች በተደለደሉበት የእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ከየምድቡ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ክለቦች (በድምሩ 16) ወደ 16 ወይንም ጥሎ ማለፍ ይገባሉ።