ዲጂታል ስዕሉ “ሶፊያ” ከጣሊያናዊው ዲጅታል አርቲስት አንድሪያ ቦናሴቶ ጋር በመተባበር የሳለችው ነው
መናገርና መዝፈንን ጨምሮ ባለብዙ ተሰጥኦ መሆኗ የሚነገርላት ሮቦት “ሶፊያ” ሳለችው የተባለለት ዲጂታል ስዕል ለሃራጅ ቀርቦ በ688 ሺ 888 ዶላር መሸጡ እያነጋገረ ነው፡፡
መቀመጫውን ሆንግ ሆንግ ባደረገው ሀንሰን ሮቦቲክስ የተሰራችው “ሶፊያ” ከጣሊያናዊው ዲጅታል አርቲስት አንድሪያ ቦናሴቶ ጋር በመተባበር የሳለችው ነው የተባለው ስዕል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) በመታገዝ የተሰራ ነው፡፡
ስዕሉ በዲጂታል የግብይት መዝገብ (Non-Fungible Token-NFT) ተሸጧልም ተብሏል፡፡
ይህ የመጀመሪያ የጥበብ ስራዋ ለሽያጭ የበቃላት ሶፊያ “ሰዎች ስራዬን ይወዱታል ብዬ አስባለሁ፤ በቀጣይም ተባብረን (ከሰዎች ጋር) ለመስራት እንችላለን” ስትል በስቱዲዮዋ በተቀረጸ ድምጽ ተናግራለች፡፡
ዲጂታል የግብይት መዝገብ (NFT) ተፈላጊነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ እየጨመረ መሆኑን የገለጸው ዘገባው መዝገቡ ላይ በተቀመጠው ዲጂታል ፊርማ አማካኝነት ማንኛውም ሰው የነገሮችን ባለቤትነት እና ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ይችላል ብሏል፡፡
በዚህ ወር ብቻ አንድ የጥበብ ሥራ በዚሁ መዝገብ በኩል በ70 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መሸጡንም ነው የጠቆመው፡፡
ሶፊያ በቀለማት ያሸበረቁ የቁም ስዕሎችን በመሳል ከሚታወቀው የ31 ዓመቱ ጣሊያናዊ ዲጂታል አርቲስት አንድሪያ ቦናቼቶ በመሆንም እንደ ኤለን መስክ ዐይነት ታዋቂ ሰዎችን መሳሏ የሚታወስ ነው፡፡
ኤለን መስክ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አማራች የሆነው ቴስላ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ነው፡፡
የሮበቷ ፈጣሪ አርቲስት ዴቪድ ሀንሰን “ሶፊያ በስራዎቿ የታዋቂው ሰዓሊ አርቲስት ቦናኬቶ ጥበቦች፣ የአርት ታሪክ እንዲሁም የራስዋ የአሳሳልና የቀለማት ጥበብ አጣምራ የያዘች በአጠቃላይ “የዝግመተ ለውጥ ተለዋዋጭ ለውጦች” ማሳየት የምትችል የውብ ጥብብ ባለቤት የሆነች አርቲስት” ሲል ገልጿታል፡፡
“በኔ ጥበብ ውስጥ የትራንስፎርመር ኔትዎርኮችን እና የዘረመል ስልተ ቀመሮችን እና ሌሎች የሂሳብ ፈጠራ ዓይነቶችን እንጠቀማለን” የምትለው ሶፊያ የእሷ ስልተ-ቀመሮች ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ያልታዩ ልዩ ልዩ ዘይቤዎች እንደሚታዩባቸውና ይህም ማሽኖቹ አዳዲስ ፈጠራ ሊያሳዩ የሚችሉ እንደሆኑ የሚያመለክት መሆኑንም ገልፃለች፡፡
ከጨረታው በኋላ ሶፊያ ካሸነፈው ተጫራች ጋር በመግባባትና ፊቱን በማጥናት በስነ-ጥበቡ ዘርፍ የመጨረሻ ደረጃ ባለ አንፀባራቂ ብሩሽ እንደምትጠበብበት ገልጻለች፡፡
ይህም “የአዲሱን ባለቤትን እና ያንን የግል መረጃዎች፤ በዚያን ጊዜና የወቅቱ ሁኔታን በሚገልፅ መልኩ ልዩ የጥበብ ሥራ ለማድረግ” የሚያስችል እንደሚሆንም ነው የሮበቷ ፈጣሪ አርቲስት ዴቪድ ሀንሰን የገለፁት።
ሶፊያ እ.ኤ.አ በ2016 ነው ይፋ የተደረገችው፡፡
ኢትዮጵያውያን የሮቦት መሃንዲሶች ሶፊያን በማዘጋጀቱ ሂደት ተሳትፎ እንዳላቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በነበረበት ወቅት መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ሶፊያ ሳዑዲ አረቢያዊ ዜግነትን ያገኘች የመጀመሪያዋ ሮቦት መሆኗም አይዘነጋም፡፡