ኢትዮጵያ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሟ አይቀሬ መሆኑን ኢኮኖሚስቶች ተናገሩ
ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ከጥቁር ገበያው ጋር እኩል እንድታደርግ ጠይቀዋል
ብሔራዊ ባንክ የብር የመግዛት አቅም ሊዳከም ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰት ነው ብሏል
ኢትዮጵያ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሟ አይቀሬ መሆኑን ኢኮኖሚስቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ሀገር የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት በሚል በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።
የወጪ ንግድን ለማበረታታት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት እንደ መፍትሔ ሲወሰድ የቆየው የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም አንዱ ነው።
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት አንድ የአሜሪካ ዶላር 27 ብር ገደማ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በባንኮች 54 ነጥብ 2 ብር በመመንዘር ላይ ሲሆን በጥቁር ገበያ ደግሞ እስከ110 ብር ድረስ እየተመነዘረ ይገኛል።
መንግስት በጦርነት እና ኮሮና ቫይረስ የተጎዳውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ከዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ብድር እና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ላይ እንደሆኑ ይገለጻል።
በቅርቡም የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከመንግስት ከፍተኛ ባለሙያዎች እና አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ እና በዋሸንግተን ውይይት ማድረጋቸው ና ጥሩ መግባባቶች ላይ ተደርሷል ማለታቸው ይታወሳል።
ይህን ውይይት ተከትሎም ዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ተመንን በጥቁር ገበያ ካለው ምንዛሬ ተመን ጋር እኩል እንዲያደርጉ ምክረ ሀሳብ እንዳቀረቡ ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያደረጋቸውን ተከታታይ ውይይቶችን አስመልክቶ የደረሱባቸውን ስምምነቶች እስካሁን ግልጽ አላደረጉም።
አል ዐይን አማርኛ በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ምንዛሬ ተመን እና እጠረቱ ጋር በተያያዘ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
ዶክተር ሽመልስ አርአያ በማክሮ ኢኮኖሚክስ ጉዳዮች ዙሪያ አማካሪ እና የጥናት ባለሙያ ናቸው፤ እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ገጥሞታል።
እጥረቱን ተከትሎም መንግስት የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሙ አይቀሬ ነው፣ እነ ዓለም ባንክም ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጡት ኢትዮጵያ ያለባትን እጥረት መጠን ስለሚያውቁ ጭምር መሆኑንም ዶክተር ሽመልስ አክለዋል።
ዓለም ባንክ አሁን ያለው የዓለም ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲቀጥል ይፈልጋል ያሉት ዶክተር ሽመልስ ስርዓቱ እንዲቀጥል ደግሞ ሀብታም ሀገራት ሀብታም ሆነው እንዲቀጥሉ የግድ ድሃ ሀገራት ከድህነታቸው እንዲወጡ አይፈለግም ብለዋል።
በብዙ ጉዳዮች እየተፈተነ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ለመፍታት ሲል መንግስት ብድር እና ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን ለማግኘት የብርን የመግዛት አቅም ያዳክማል፣ ለዚህ ደግሞ የውጪ ንግስትን ለማበረታታት የሚል ስም ይሰጣልም ብለዋል።
ከዚህ በፊት የተደረጉ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ውሳኔዎች የኑሮ ውድነትን ከማባባስ፣ የሐብት ሽሽትን ከመፍጠር እና የንግድ ሚዛንን ከማዛባት ውጪ ጥቅም አለማስገኘታቸውንም አክለዋል ዶከተር ሽመልስ።
እንደ ዶክተር ሽመልስ ገለጻ የሀገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብን ማዳከም የሚሰራው እንደ ጃፓን እና ቻይና ያሉ ሰፊ ወደ ውጪ ሊላኩ የሚችሉ ምርቶች ላሏቸው ሀገራት ብቻ እንጂ እንደ ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጪ ለሚልኩ ሀገራት አይደለም።
- የፋይናንስ ተቋማት ጠቅላላ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ ገለጸ
- ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር ለሚኖር ውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቀረበ
መንግስት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ገቢ በላይ ብር ማተሙን ካላቆመ የኢኮኖሚ ቀውሱ ይጨምራል ያሉት ደግሞ ሌላኛው ኢኮኖሚስት አቶ መቆያ ከበደ ናቸው።
አቶ መቆያ እንዳሉት “የመንግስት ገቢ እና ወጪ አለመመጣጠን፣ ቅንጡ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ማፍሰስ እና መንግስት ራሱ የውጭ ምንዛሬ ከጥቁር ገበያ እየገዛ መሆኑ በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን እያባባሱ ናቸው” ብለዋል።
“በኢትዮጵያ ማንኛውም ሰው የየትኛውንም ሀገራት መገበያያ ብር እስካለው ድረስ ከጥቁር ገበያ እየገዛ ነው” የሚሉት አቶ መቆያ ይህ የሚያሳየው የውጭ ምንዛሬ ከገበያው ላይ መኖሩን ነው፣ ኢኮኖሚው የውጭ ምንዛሬ እያመነጨ ነው፣ ችግሩ የአያያዝ እንጂ የአቅርቦት አይደለም ሲሉም አክለዋል።
በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸውን በባንክ አለመላካቸው፣ የውጭ እዳ ከፍተኛ መሆን፣ በኮሮና ቫይረስ እና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከውጭ ሀገራት ጎብኚዎች የሚገኘው ገቢ ማሽቆልቆል፣ የማዕድናት እና ሌሎች የንግድ ስራዎች ህገ ወጥነት መስፋፋት መንግስትን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደዳረገውም ተገልጿል።
መንግስት የገጠመውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ኢኮኖሚውን በውድድር ለይ የተመሰረተ ማድረግ እና የውጭ ምንዛሬ ተመኑን በባንኮች እና በጥቁር ገበያ ያለውን እኩል ማድረግ ይኖርበታልም ብለዋል።
በኢኮኖሚው አስገዳጅነትም ሆነ በእነ ዓለም ባንክ ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሙ እንደማይቀርም አቶ መቆያ ግምታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ከሰሞኑ የብርን የመግዛት አቅም ሊዳከም ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰት ነው ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።
የባንኩ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ፥ " እስከዛሬ ድረስ በአንድ ጊዜ የሚደረግ የብር የምንዛሬ ተመን ለውጥ ለማድረግ የተደረገ ውይይትም፣ የተወሰነ ውሳኔ ፈፅሞ የለም " ብለዋል።
የብር የምንዛሬ ለውጥን በተመለከተ የተደረገ ውይይት ወይም የተወሰነ ውሳኔ የለም ያሉት አቶ ማሞ ዜጎች በተረጋጋ ሁኔታ በገበያ ስርዓቱ እንዲጠቀሙ ማሳሰቢያ መስጠታቸውም ይታወሳል።