የደራው የምንዛሬ ጥቁር ገበያ በኢትዮጵያ
ለጥቁር ገበያው መድራት “የዶላር እጥረትና የገበያው ሁኔታ ብቻ በምክንያትነት ሊጠቀሱ አይችሉም” የሚሉት ዶ/ር አጥላው በበኩላቸው “መንግስት፤ ባለስልጣናቱ ጭምር ምን እየሰሩ እንደሆነ አለማወቃችን ሁኔታውን አባብሶታል” ይላሉ
“ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታው ሰው ያለውን መሸሸግና በምንዛሬ መያዝ የሚል ስነ ልቦና እንዲያዳብር ማድረጉ ጥቁር ገበያውን አድርቶታል”-አቶ ዋሲሁን በላይ፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ
በኢትዮጵያ የውጭ ሃገራት ገንዘቦችን ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከሰጣቸው ባንኮች ውጭ መገበያየትም ሆነ ማገበያየት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
ባንኩ ከፈቀደው መጠን ውጭ ገንዘቦቹን ይዞ መገኘትም ሆነ ማዘዋወርም አይቻልም፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከባንክ ውጭ ያለው የገንዘቦቹ የግብይት ሁኔታ ግን አሳሳቢ ነው፡፡ በትይዩነት በሚጠቀሰው የገንዘቦቹ ጥቁር ገበያ (ብላክ ማርኬት) ሁኔታም ከእለት ወደ እለት እየተጠናከረ ይገኛል፡፡
ገንዘቦቹ የሚመነዘሩበት የዋጋ ሁኔታ እንደየአካባቢው እና ከተሞቹ ቢለያይም አዲስ አበባ ላይ የዛሬ አንድ ወር ገደማ ከ60 እስከ 68 ብር ድረስ ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካ ዶላር ዛሬ እስከ 72 ብር ድረስ እንደሚመነዘር የአል ዐይን አማርኛ የመረጃ ምንጮች አመልክተዋል፡፡
የምንዛሬ ገንዘቡ ምናልባትም መንዛሪው በሚያመጣው የውጭ ገንዘብ መጠን ላይ ተመስርቶ የሚለያይ ነው፡፡
ጥቁር ገበያው በተለይ በአዲስ አበባ ያለው ጥቁር ገበያ የደራው የውጭ ሃገራት ገንዘቦችን የመቆጣጠር ያልተማከለ ስልጣን ባለው ብሔራዊ ባንክ አቅራቢያ የመሆኑ ተቃርኖ ደግሞ አግራሞትን የሚያጭር ነው፡፡
የውጭ ገንዘቦቹ በባንክ ከሚመነዘሩበት ዕለታዊ ዋጋ ከፍ ባለ ሁኔታ ከብር ለእጥፍ በቀረበ የምንዛሬ ዋጋ መመንዘራቸው ብዙዎችን አሳስቧል፡፡ የኑሮ መወደድ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው በሚል ብዙዎች ስጋታቸውን ሲገልጹም ይደመጣሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) በጥቁር ገበያው ያለውን ይህን የምንዛሬ ዋጋ ንረት “ከዚህ አንጻር ነው ብሎ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው” ይላሉ፤ የዶላር እጥረትና የገበያው ሁኔታ ብቻ በምክንያትነት ሊጠቀሱ እንደማይችሉ በመጠቆም፡፡
“መንግስት ያወጣቸው ህጎች በወጉ ተተግበረው ሁኔታውን ተቆጣጥሮት ቢሆን ኖሮ የገበያውን ሁኔታ በምክንያትነት እንጠቅስ ነበር” የሚሉት ዶ/ር አጥላው አሁን ያለው ሁኔታ ለመተንበይ ጭምር እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
ይህ ደግሞ “መንግስት ያልደረሰባቸው ወይም ሊደርስባቸው ያልፈለጋቸው በሚስጥር የሚካሄዱ ነገሮች በመኖራቸው ነው” ነው የሚሉት መምህሩ፡፡
“መንግስት፤ ባለስልጣናቱ ጭምር ምን እየሰሩ እንደሆነ አናውቅም” የሚሉም ሲሆን “የወጪ ንግድ እየጨመረ ነው በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) እያደገ ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት የጥቁር ገበያው መድራት ማለት እኛ በማናውቀው ስውር መንገድ የሚሰራ ስራ አለ ማለት ነው” ሲሉም ያስቀምጣሉ፡፡
የጥቁር ገበያው መድራት እና የውጭ ገንዘቦች የምንዛሬ ተመን መጨመር ከምጣኔ ሃብታዊ ምክንያት ይልቅ “በሻጥር” እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህን የገለጹት የባንኩ ምክትል ገዢ እና ቺፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ችግሩ በተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ምላሽ እንደሚሰጠውና የፖሊሲ አማራጮች እንደሚፈለጉለትም ተናግረው ነበር፡፡
ይህ ግን ለምጣኔ ሃብት መምህሩና ተመራማሪው እምብዛም አይዋጥም፡፡
የጥቁር ገበያው መድራት “ ‘የምንዛሬ ዋጋ የናረው በአሻጥር ነው’ ብለው የሚነግሩን ባለስልጣናት ጭምር አካል የሆኑበት ሚስጥራዊ ህገወጥ ስራ እንዳለ አመላካች ነው” ሲሉም ነው ዶ/ር አጥላው የሚናገሩት፡፡
በዚህም መንግስት ገበያውን ሊቆጣጠረውና ዜጎችን በየእለቱ እየመጨረ ከሚሄድ የኖሮ ፈተና ለመታደግ አልቻለም፡፡
ይህ በዚሁ ከቀጠለ የብር የመግዛት አቅም ከዚህም በላይ ይደክምና ከባድ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን እንደ ሃገር ሊያስከትል ይችላል፡፡
ዶ/ር አጥላው ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ሊኖራቸው ቢችልም “ንረቱ እና የጥቁር ገበያው መድራት ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ እያደገ የመጣ እንጂ ዛሬ የጋጠመ አይደለም” የሚሉም ሲሆን በመንግስት “የአስተዳደርና የአፈጻጸም ሁኔታዎች ላይ በሚመሰረት ተግባር ብቻ” ሊረጋጋ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የጥቁር ገበያው መድራት እና የዋጋው መናር “ምክንያታዊ አይደለም” የሚያስብለው “በሰው ሰራሽ ችግሮች እና ሻጥሮች ሲቸገር ነው” የሚሉት ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው ኢኮኖሚው ምንዛሬ ለማቅረብ አለመቻሉን ተከትሎ ያጋጠመ ነው ይላሉ፡፡
“እስከ 18 ቢሊዬን ዶላር እናወጣበታለን” የሚሉት የኢትዮጵያ “ሸማች ምጣኔ ሃብት” በዚህ መጎዳቱንም ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች እና በማዕድናት የወጪ ንግድ፣ በቴሌ የፕራይቬታይዜሽን ሂደት በሌሎች የምንዛሬ ግኝት መንገዶች ጭምር የተሻለ ገቢን አግኝታለች፡፡ ሆኖም ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታው መንግስትን ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎታል፡፡
ከዚህም በላይ ሁኔታው “ሰው ያለውን መሸሸግና በምንዛሬ መያዝ የሚል ስነ ልቦና” እንዲያዳብር እንዳደረገውም ነው ባለሙያው የሚናገሩት፡፡
ይህ እየደራ የመጣ የጥቁር ገበያ ሁኔታ “ምጣኔ ሃብትን ሽባ በማድረግ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥና የሚያናጋ ነው”እንደ ባለሙያው ገለጻ፡፡
በመሆኑም እንቅስቃሴውን መግታትና ማክሰም በአጭር ጊዜ የሚሳካ የቤት ስራ ባይሆንም ምክንያቶቹን በመለየት፣ ለፖለቲካዊ ችግሮች አፋጣኝ እልባቶችን በመስጠት እና በገቢ ንግድ ላይ ገደቦችን በመጣል መቆጣጠር ይገባል፡፡
የምንዛሬ አቅርቦትን ሊያሳደጉ የሚችሉ ተግባራትን በማከናወንና ክምችቱን በማሳደግ ስር ነቀል ለውጦችን ለማምጣት እንደሚቻልም አቶ ዋሲሁን ተናግረዋል፡፡