ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ ልታደርግ ነው
ሀገሪቱ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ትግበራ መግባቷን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል
አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአቷን እንድታሻሽል ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወቃል
ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት ተግባራዊ ልታደርግ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጽህፈት ቤት ከጥቂት ስአት በፊት ባወጣው መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ትግበራ መግባቷን አመላክቷል።
በ2011 ወደ ትገበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ያስገኘውን ውጤት በዝርዝር ያነሳው መግለጫው፥ በቅርቡ የጸደቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀሪ የማክሮ ኢኖኮሚ ማሻሻያ ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝ አብራርቷል።
ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ትግበራ መግባቷ ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ነጠላ አሀዝ የዋጋ ግሽበት እንዲኖራት ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።
ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ትግበራ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁና የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ድርድሮች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ነው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መግለጫ ያወሳው።
በዚህም መንግሥት ባስቀመጣቸው ዋና ዋና የማከሮ ኢኮኖሚ ዓላማዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ቅደም ተከተል መሠረት ስምምነት ላይ መደረሱንና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ በዓለም ባንከ እና በሌሎች የልማት አጋሮች እንደሚደገፍም ጠቁሟል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ለማስተካከል፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ፣ የ የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግና የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚያግዝም ነው ያነሳው።
በአለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ይደገፋል የተባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ከሚያካትታቸው ዋና ዋና የፖሊሲ እርምጃዎች መካከል የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአትን በገበያ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያደርገው አንዱ ነው።
የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የማድረጉ ሂደት በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ መዛባት ለማስተካከልና የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።
የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)ን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ የብር የመግዛት አቅምን እንድታዳክም አልያም የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአቷ በገበያ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሰኔ ወር መጨረሻ ከህዝብ እንደራሴ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ጋር የምታደርገው ድርድር ከተሳካ 10 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ታገኛለች ማለታቸው ይታወሳል።
ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ከአለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ድጋፍን የሚያስገኝ ቢሆንም የዋጋ ግሽበትን እንደሚያስከትል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ለሚያስከትሉት አሉታዊ ተጽዕኖ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን ጉዳዮችም ዘርዝሯል።
ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ድጎማና ማሻሻያዎች ለተወሰኑ ጊዜያት እንደሚደረግና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን መንግስት በከፈል እንደሚደጉምም ነው መግለጫው የጠቆመው።