ኢትዮጵያ H5170 በሚል ስያሜ ለጡት ካንሰር ታማሚዎች የሚሰጠው መድሃኒት ጥቅም ላይ እንዳይውል አሳሰበች
መድሃኒቱ በህገወጥ መንገድ በገበያ ላይ መኖሩን የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታውቋል

ጥቅም ላይ እንዳይውል የተባለው መድሃኒት በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እንዳልገባ ተገልጿል
ኢትዮጵያ H5170 በሚል ስያሜ ለጡት ካንሰር ታማሚዎች የሚሰጠው መድሃኒት ጥቅም ላይ እንዳይውል አሳሰበች፡፡
ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ ከሆፍማን ሮቼ ኢትድ የንግድ ተወካይ ጽህፈት ቤት የተላከውን ማስታወቂያ እና በኬኒያ ፒፒቢ የተሰራጨውን የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ ዋቢ ማድረጉን ገልጿል።
በዚህ መሠረት ባለሥልጣኑ በጥያቄ ውስጥ ያሉትን ምርቶች የገበያ ፈቃድ በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ግምገማ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን ሄርሴፕቲን 440 ሚ.ግ ወደ ኢትዮጵያ ለገበያ ለማቅረብ የተመዘገበ ተመዝግቧል ብሏል፡፡
መድሃኒቱ የምርት ስሙ ሄርሴፕቲን 440 ሚሊግራም የሆነ፣ ጄንቴክ ኢንክ በተባለ አምራች ኩባንያ በአሜሪካ የተመረተ፣ የፈቃድ ባለቤት ኤፍ ሆፍማን ላ ሮቼ የተሰራበት መንገድ ደግሞ ፓውደር የሆነ በመርፌ መልክ የሚሰጥ ነውም ተብሏል፡፡
እንዲሁም መድሃኒቱ የባች ቁጥር 05830083 የሆነ በኬኒያ ሀሰተኛ መድኃኒት መሆኑን የተረጋገጠና ከኢትዮጵያ በባች ቁጥር H5170 በሚል የተረጋገጠ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
የመድኃኒቱ ምርት በተፈቀደላቸው አስመጪዎችና አከፋፋዮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዳልመጣ ባለሥልጣኑ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ነገር ግን ሮቼ ኬኒያ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ አንድ ታካሚ ካልተረጋገጠ ምንጭ የተገዛውን የሄርሴፕቲን 440 ሚ.ግ መግዛቱ የተረጋገጠ ሲሆን የመድኃኒቱ ማቀፊያ ሳጥን በከፊል የሚያሳየው ምስል እና የመድኃኒት ጠርሙስ ምስል ቁጥር H5170 የተረጋገጠ ሐሰተኛ የመድኃኒት ምርት በኬኒያ ውስጥ እየተሰራጨ እንደሆነ መረጋገጡን ባለስልጣኑ በመግለጫው ለይ ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በ10 ሺህ ሰዎች ላይ ጥላው የነበረውን የጉዞ እገዳ አነሳች
የባለ ስልጣኑ መግለጫ አክሎም ከላይ በዝርዝር የመድኃኒቱ ምርት መረዳት የምንችለው ምንም እንኳን ይህ የተጭበረበረ ባች ምርት በኬኒያ ቢታወቅም ምናልባት ወደ ኢትዮጵያ የተሰራጨው በኢ-መደበኛ ገበያ ሊሆን እንደሚችል በህብረተሰቡ ላይም ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ከስርጭት ውስጥ መለየት እና ማስወገድ አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡
በመሆኑም መድኃኒት አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች፣ የችርቻሮ ነጋዴዎች እና ጤና አጠባበቅ አቅራቢዎች የሀሰተኛ ወይም የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመድኃኒት ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ እንዳይከፋፈሉ፣ እንዳይሸጡ እና እንዳይገዙ እንዲሁም ከአቅርቦት ሰንሰለት ጋር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባለስልጣኑ አሳስቧል።