መንግስት በተቋረጡ የግንባታ ፕሮጀክቶች ምክንያት ለ17 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ መዳረጉ ተገልጿል
የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ተቋማትን የበጀት ኦዲት ግኝት ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው በፌደራል መንግሥት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ሲሆን ህግ ተጥሶ ስራ ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን ያላግባብ እንዲይዙ ተደርጓል ተብሏል፡፡
የስራ ተቋራጮች ከዚህ በፊት የነበራቸው የስራ አፈጻጸም ሳይታይ በሌሎች የግንባታ ጨረታዎች ላይ እንዲወዳደሩ እና እንዲገነቡ መደረጉን ዋና ኦዲተሩ አስታውቋል።
11 ቢሊዮን ብር ገደማ ዋጋ ያላቸው 12 የግንባታ ፕሮጀክቶች ለሁለት የስራ ተቋራጮች መያዛቸው የህግ ጥሰት መፈጸሙ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል
የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ስድስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድር 50 ቢሊዮን ብር መድረሱንም ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ላጥ ጠቅሷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ 16 ተቋማት በድምሩ 19 ቢሊዮን ብር ያልተጠቀሙበት በጀት እንደተገኘም ተገልጿል፡፡
የመንግስት ተቋማት በቅጣት መልክ ከካዝና በማውጣት ለግለሰቦች ከፍለዋል የተባለ ሲሆን በተለይም በጉምሩክ ኮሚሽን የጅግጅጋ ቅርንጫፍ 10 ሚሊዮን ብር ለግለሰብ ከፍሏል ተብሏል፡፡
የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከገንዘብ ሚኒስቴር እውቅና ውጪ ከፓስፖርት አገልግሎት ጠያቂዎች 17 ሚሊዮን ብር በህገወጥ መንገድ ሰብስቧል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 9 ሚሊዮን ብሩን ለሰራተኞች የበዓል ስጦታ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዳዋለው ተገልጿል፡፡