የኢትዮጵያ መንግስት በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች 248 ንጹሃን ተገድለዋል - ተመድ
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች 70 በመቶዎቹ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መፈጸማቸውንም ድርጅቱ ገልጿል
ተመድ መንግስት በአማራ ክልል የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለማራዘሙን እደግፋሁ ብሏል
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች 70 በመቶዎቹ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መፈጸማቸው ተገለጸ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሀገሪቱን ሰላም እና አንድነት እያናጉ ነው ብለዋል፡፡
“ሁሉም ተፋላሚዎች ውጊያ እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ” ያሉት ኮሚሽነሩ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱም አሳስበዋል፡፡
ተፋላሚ ወገኖች ንጹሃንን ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው፣ ይህን የተላለፉት ወደ ህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡
አሁን እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ባሳለፍነው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ እንደጨመረም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጦር አስወጣለሁ ማለት እና የኢትዮጵያ ምላሽ
መንግስት ካሳለፍነው ነሀሴ እስከ ታህሳስ ባሉት አምስት ወራት ውስጥ በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች ምክንያት 248 ንጹሃን ሰዎች ተገድለዋል ያለው የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች አይነት የህዝብ መገልገያ ተቋማት ወድመዋልም ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 594 የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ በመንግስት 22 ከመቶ አካባቢ ደግሞ በግጭቱ ተሳታፊዎች እንደተፈጸሙ ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ አክሎም የፋኖ ታጣቂዎች 52 ንጹሃንን እንደገደሉ የገለጸ ሲሆን የግለሰቦችን ንብረት ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎችን፣ ተቋማትን እና የመንግስት ተቋማት ሃላፊዎችን አጥቅተዋልም ብሏል፡፡
በአማራ ክልል ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከ10 ወራት ቆይታ በኋላ መነሳቱን የገለጸው ኮሚሽኑ መንግስት የወሰውን ውሳኔ እንደሚደግፍም አስታውቋል፡፡
ይሁንና መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩ ዜጎችን በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቅ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡