ኢትዮጵያ ላለባት የዓለም ዋንጫ ማጣያ ለተጫዋቾች ጥሪ አደረገች
ኢትዮጵያም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 7 ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ጋር ነው የተደለደለችው
የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ፣ የአፍሪካ ሀገራት የማጣሪያ ውድድር ከፊታችን መስከረም ወር ጀምሮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል
ኢትዮጵያ ላለባት ለዓለም ዋንጫ ማጣያ ለተጫዋቾች ጥሪ ማደረጓን የኢትዮጵየ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከዚምቧቤ አቻው ላለበት የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ28 ተጫዋቾች የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ማድረጋቸውን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሰረት ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች አስራት ቱንጆ ፣ አማኑኤል ዮሀንስ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ ዊሊያም ሰለሞን እና አቡበከር ናስር ከኢትዮጵያ ቡና፤ ጀማል ጣሰው እና ረመዳን የሱፍ ከወልቂጤ ከነማ፤ መሱድ መሀመድ ከጅማ አባጅፋር ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
እንዲሁም ሱሌማን ሀሚድ ፣ ምኞት ደበበ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ሀይደር ሸረፋ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሪ ሲደረግላቸው፤ ተክለማሪያም ሻንቆ ከሲዳማ ቡና፣ ፍሬው ጌታሁን ከድሬዳዋ ከተማ፣ ደስታ ዮሀንስ ከሀዋሳ ከነማ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ያሬድ ባዬ ፣ አስቻለው ታመነ፣ ይሁን እንደሻው ፣ ሀብታሙ ተከስተ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ሽመክት ጉግሳ እና ሙጂብ ቃሲም ከፋሲል ከነማ ጥሪ ሲደረግላቸው፤ ፋሲል ገ/ሚካኤል፣ ኤፍሬም አለሙ እና መናፍ አወል ከባህር ዳር ከነማ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅቱን አዳማ ላይ የሚየደርግ መሆኑም የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ጥሪ የተደረገላቸው የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የፊታችን እሁድ ነሓሴ 2 ቀን 2013ዓ.ም በካፍ አካዳሚ ሪፖርት የሚያደርጉ መሆኑም ታውቋል።
የአፍሪካ ሀገራት በኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በ10 ምድቦች ተከፋፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በምድብ 7 ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ጋር የምትጫወት ይሆናል።
ከየምድቡ 1ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ 10 ብሔራዊ ቡድኖች ለሁለት ተከፍለው በሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ውድድር በ2022 የዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ ሀገራ እንደሚለዩም ተገልጿል።
ለ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ፣ የአፍሪካ ሀገራት የማጣሪያ ውድድር በቀጣዩ ዓመት መስከረም፣ ጥቅምት እና ህዳር እንዲሁም የካቲት ወር ላይ እንዲካሄዱ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የአፍሪካ ሀገራት የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች ካሳለፍነው ሰኔ ወር ጀምሮ እንደሚያካሂዱ ከዚህ ቀደም የወጣው መርሃ ግብር ያመለክት ነበር።
ሆኖም ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባካሄደው አስቸኳይ ስበስባ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ባጋጠሙ ፈተናዎች እንዲሁም ለሁሉም ተሳታፊ ሀገራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በሚል የውድድር ጊዜውን ለማራዘም የወሰነው።