ፋሲል ከነማ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው 4 የሊጉ ጨዋታዎች ሲቀሩት ነበር
ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የ2013 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በዛሬው እለት አነሳ።
ፋሲል ከነማ በዛሬው እለት ከሀዋሳ ከተማ ጋር በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የ23ኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያካሄደ ሲሆን፤ ጨዋታውም 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መርሃ ግብር ከጠናቀቀ በኋላ ክለቡ የመጀመሪያውን የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን በ2ሺ ደጋፊዎቹ ፊት አንስቷል።
ፋሲል ከነማ (ዐፄዎቹ) የ2013 ዓ.ም የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸውን አራት የሊግ ጨዋታዎች እየቀሩ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።
ፋሲል ከነማ ፕሪምርሊጉን በ53 ነጥብ በመምራ ነው በዛሬው እለት ዋንጫውን ያነሳ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቡና በ37 ነጥብ፣ በሰታ ከነማ በ36 ነጥብ፣ ሀዲያ ሆሳእና በ35 ነጥብ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በ34 ነጥብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ፋሲል ከነማ በኮሮና ምክንያት በተቋረጠው በባለፈው የውድድር ዓመትም ዋንጫውን ለማሸነፍ ተቃርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዓመቱ ውድድር ሳይጠናቀቅ እንዲቋረጥ በመወሰኑ ያለፈው ዓመት ማንም ሻምፒዮን ሳይሆን ተዘግቷል፡፡