የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትግራይ ክልል ምርጫ ጋር በተያያዘ የመጨረሻ ያላቸውን የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች አሳለፈ
ክልሉ ምርጫን በሚመለከት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደማይፀኑ እና ተፈፃሚነት እንደሌላቸውም ገልጿል
“ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር አለኝ” ያለው ምክር ቤቱ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቋል
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትግራይ ክልል ምርጫ ጋር በተያያዘ የመጨረሻ ያላቸውን የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች አሳለፈ
የትግራይ ክልል አካሂደዋለሁ ካለው ምርጫ ጋር በተያያዘ ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በዝግ ሲወያይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀ፡፡
ክልሉ ያወጣው የምርጫ አዋጅ እና አዋጁን መሰረት አድርጎ ያቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን፣ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና የፈፃማቸው ተግባራት የምክር ቤቱን ውሳኔን ወደ ጎን በመተው የተደረጉ ናቸው ያለው ምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ እንዲሰጥበት በሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተጣርቶ ለመጨረሻ ውሳኔ ለምክር ቤቱ በሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች በኩል በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት ማድረጉን ገልጿል፡፡
ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር ያለው መሆኑንና “ህገወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም” ብሎ እንደሚያምን የገለጸም ሲሆን “በቀጣይም ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት” መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ እና የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች በመጥቀስ የትግራይ ክልል እያካሄደ ካለው ህገወጥ ምርጫ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብት አለማክበር ተቀባይነት የሌለውና ሊታረም የሚገባው መሆኑ አስቀምጧል፡፡
ከዚህም ባሻገር ክልሉ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ምክር ቤቱ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ያስተላለፈውን ውሳኔ እና የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በደብዳቤ ሕገ መንግስቱና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንዲከበር የሰጡትን ማሳሰቢያ አለመቀበሉ ኢ-ሕገ መንግስታዊ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ ክልሉ ያወጣው የምርጫ አዋጅ ከሕገ መንግስቱ አንቀጽ 55(15) እና አንቀጽ 55(2) (መ) ጋር ይቃረናል፣ያቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ስልጣን ይጥሳል፤ የክልሉ ምክር ቤት አስፈጻሚ አካላትና ኮሚሽኑ ምርጫን በሚመለከት ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት በሙሉ ድምጽ የመጨረሻ ያላቸውን የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡