የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥንቃቄ እያደረገ ወደ ቻይና በረራውን እንደሚቀጥል አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ገለጹ፡፡
ከኮሮና ቫይረስ እና የቻይና በረራ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ኮሮና ቫይረስ ቻይና ላይ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ አየር መንገዱ የቅርብ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በተለይም የአሜሪካና አውሮፓ ጥቂት አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ከማቆማቸውና ከመቀነሳቸው ውጭ አብዛኛው የዓለማችን አየር መንገዶች መደበኛ በረራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
በአፍሪካ አቻ የሌለው የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ሀገሪቱ የሚያደርገውን በረራ ያለምንም ማቋረጥ እኝደቀጠለ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ በረራውን መቀጠሉ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑም ይታወቃል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም፣ በረራ ማቆም ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መፍትሔ እንደማይሆን ነው የተናገሩት፡፡ በረራ ማቆምና ቻይናን ማግለል የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት ይልቅ ህገወጥ እንቅስቃሴን በማበረታታት እንደሚያባብሰው የዓለም ጤና ድርጅት መግለጹን በማስታወስ የኢትዮጵያ አየር መንገድም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ በረራውን እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡
አቶ ተወልደ በረራ ማቆም መፍትሔ አለመሆኑን ለማስረዳት ምሳሌዎችን ተጠቅመዋል፡፡
የአየር መንገድ የሌላት ናይጄሪያ የኮሮና ቫይረስ ምልክት የታየባት ሀገር ስትሆን ከአፍሪካ ወደ ቻይና በረራ ካቆሙት አንዱ የኬኒያ አየር መንገድ ቢሆንም ድርጊቱ በሀገሪቱ ምልክቱን ከመታየት አላገደም ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡
የብሪታኒያ አየር መንገድም ወደ ቻይና በረራ ማድረግ ቢያቆምም በሀገሪቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተዋል፡፡ የሀገሪቱ አየር መንገድ ወደ ቻይና አይብረር እንጂ የቻይና ሶስት አየር መንገዶች ወደ ብሪታኒያ የሚያደርጉትን በረራ አላቋረጡም፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ ቢያቆም እንኳን የቻይናን ጨምሮ ሌሎች አየር መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን በረራ አያቆሙም፡፡ በመሆኑም ጥንቃቄ ማድረግ እንጂ በረራ ማቆም ምንም መፍት ሔ አያመጣም ነው ያሉት አቶ ተወልደ በማብራሪያቸው፡፡
አብዛኛው የአየር ትራንስፖርቶች የሚካሔዱት በቅብብሎሽ/ጠለፋ (ትራንዚት) በመሆኑ ወደ ቻይና የማይበሩ አየር መንገዶችም ጭምር ከሌሎች ሀገራት በትራንዚት ቻይናውያንን ከቦታ ቦታ ማዘዋወራቸው አይቀርም፡፡ ዛሬ ወደ ቻይና በረራ ማድረግ ብናቆም ከሌሎች ሀገራት ቻይናውያንን ማምጣታችን አይቀርም ያሉት አቶ ተወልደ እናም በተጠላለፈ እና በተሳሰረ ዓለም ውስጥ በረራ ማቆም እና ማግለል መልኩን ቢቀይር እንጂ የማይቻል ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በየጵያ በቫይረሱ ከተጠረጠሩ ግለሰቦች አንዱ በሌላ አየር መንገድ የመጣ መኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን የማያቆምበት ሌላው ምክኒያት በቻይናና አፍሪካ መካከል በሚደረገው በረራ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወጣው አየር መንገድ እርሱ በመሆኑ ነውም ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡
አየር መንገዱ ፓን አፍሪካኒዝምን የሚያቀነቅን መሆኑን ያወሱት አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም አፍሪካን እርስ በእርስ እና ከሌላው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ለአህጉሪቱ ጥቅም መቆሙን በተግባር በማረጋገጥ አፍሪካዊነቱን ማንጸባረቁን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ለዚህም አሉ አቶ ተወልደ ለዚህም አየር መንገዱ በአስቸጋሪ ወቅቶችም አህጉሪቱን ማገልገሉን ይቀጥላል፡፡
የኢቦላ ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪካ በተከሰጠበት ወቅት ወደ ሀገራቱ በረራውን ሳያስተጓጉል መቀጠሉን፤ እንዲሁም በአንጎላ ከአስርት ዓመታት በፊት በነበረው የእርስ በርስ ግጭት ወቅት በብቸኝነት ወደ ሀገሪቱ ሲበር የነበረ መሆኑንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ይሁንና አሁን ወደ ቻይና በሚደረገው በረራ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የዓለም ጤና ድርጅትን መርህ በመከተል በአውሮፕላን ውስጥ፣ በመነሻና መድረሻ ስፍራዎች ሁሉ አየር መንገዱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ከጤና ሚኒስቴር እና የዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የኮሮና ቫይረስ መመሪያ መሳሪያ ለማምጣትም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ገልጸዋል፡፡