ኢትዮጵያ ለህዳሴው ግድብ የሩሲያን የቴክኒክ ድጋፍ ልትጠይቅ ትችላለች- አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ
አምባሳደሩ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከሞስኮ ጋር እንነጋገርበታለን ብለዋል
የህዳሴው ግድብ ግንባታ 88 በመቶ ተጠናቋል
ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድብ የውሃ መጠን ማወቅ ጋር በተያያዘ ሩሲያን የቴክኒክ ድጋፍ(የውሃ መጠን አቅርበው የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች) ልትጠይቅ እንደምትችል አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ተናገሩ፡፡
አምባሳደሩ ከሩሲያው “ስፑትኒክ” ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በሩሲያ በኩል ሁልጊዜ የቴክኒክ ድጋፍን ለማድረግ ፍላጎት አለ፤ ኢትዮጵያም በደስታ ትቀበለዋለች።
አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በጥያቄው ላይ ከሞስኮ ጋር የምንነጋገርበት ይሆናል ..በእነሱ በኩል ሀሳቡ እንዳለ አውቃለሁ፤ ጥሩ ይመስለኛል” ብለዋል፡፡
አምባሳደር አለማየሁ ቀደም ሲል ከዚሁ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የህዳሴው ግድብ ግንባታ 88 በመቶ መጠናቀቁን እና ስራው በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚጠናቀቅ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
“ይህንን ግድብ የምትመራው ኢትዮጵያ ብቻ ናት” ሲሉም ነበር ያሳሰቡት፡፡
የአባይ ውሃ ብቅረቡ ለሶስተኛ ጊዜ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አናት ላይ መፍሰስ መጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ እንደሚሆን የሚጠበቀው የህዳሴ ግድብ ከፍታው 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ ደግሞ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ፈሶበት ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል የተባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ነሃሴ 12 ቀን፤2022 ሶስተኛው ሙሌት ይፋ በተደረገበው በቤንሻንጉል ጉባ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ዘንድሮ 22 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ ውሃ መያዝ የሚያስችል ስራ መሰራቱን መናገራቸው አይዘነጋም።
“የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የውሃ እጥረት እንዳያግጥም ኢነርጂ እያመነጨን በታቸኛው ቦተም አውትሌት በኩል ውኃ በከፍተኛ ሁኔታ አንድም ቀን ሳይቋረጥ እንዲሄድ እየተደረገ ነው”ም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።