ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ላደረጉት ጥረት አመሰገኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የህዳሴ ግድብን የኃይል ማመንጨት ኃራ አስጀምረዋል
ቀዳማዊ ሀይለስላሴ፣መለስ ዜናዊ እና ሀይለማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመሰገኑ መሪዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ላደረጉት ጥረት አመሰገኑ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል 375 ሜጋዋት ማመነጨት የሚያስችለው እንዱ ተርባይን ሀይል ማመንጨት ጀምሯል።
በዚህ የሀይል ማመንጨት መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ግድቡ እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎችን በስም ጠቅሰው አመስግነዋል፡፡
ቀዳማዊ ሀይለስላሴ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች መለስ ዜናዊ እና ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ ለህዳሴው ግድብ እውን መሆን ላደረጉት የአመራር ሚና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስግነዋል።
“መሪዎቹ የተለያየ የፖለቲከሰ እሳቤ ቢኖራቸውም፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ተነስተው የኢትዮጵያ መሪ ቢሆኑም ኢትዮጵያን የሚጠቅም ትልቅ ፕሮጀከትን እውን እንዲሆን ብዙ ደክመዋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትት አብይ አህመድ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዚህ መሪዎች በተጨማሪም የቀድሞወ የህዳሴው ግድብ ስራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለን ጨምሮ የቀድሞው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሮች አቶ አለማየሁ ተገኑ እና ዶክተር ኢንጅነር በቀለን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችንም አመስግነዋል፡፡
“የግድቡ ሀይል ማመንጨት መጀመር ለአኅጉራችን እንዲሁም አብረናቸው ሠርተን በጋራ ለመጠቀም ለምንሻ የታችኛው ተፋሰስ አገራት የምሥራች ነው። ዐባይ ወንዛችንን ሀገራችንን አልምቶ ጎረቤቶቻችንን ሊያረሰርስ ጉዞውን ቀጥሏል” ብለዋል።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ወንድም የሱዳን እና የግብጽ ህዝቦች ዛሬ የተጀመረው ኃይል የማመንጨት ስራ ለእናንተም በረከት ነው እና እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
“ባልተገባ ሁኔታም ቢሆን ለፈጠራችሁት ተጽእኖ እና ፈተናም ለመሰግናችሁ እወዳለሁ፤ መላው የዓለም ህዝብ እንዲገነዘብ የምፈልገው፤ ይህ ውሃ እንደምታዩት ኃይል እያመነጨ ወደ ሱዳን እና ግብጽ የሚሄደ እንጂ፤ ሲነገር እንደነበረው ኢትዮጵያ ውሃውን ገድባ ወንድም የግብጽ እና የሱዳን ህዝብን የማስራብ እና የመስጠማት ፍላጎት እንደሌላት በተግባር ያሳየንበት ነው፤ ለዚህም ደስ ብሎናል ብለዋል።“
ዛሬ የመጀመሪያው ነው፤ ከዛሬ በኋላ በየጊዜው ቀሪ ተርባይኖችን ወደ ስራ እየገቡ ይሄዳሉ፤ ከዚህ በኋላ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መነታረክ ትተን፤ ራሳችንን፣ ከግብጽ እና ከሱዳን እንዲሁም ሌሎችንም ሀገራት በሚጠቅም ሁኔታ በጋራ እንድንሰራ ጥሪ አቀርባለሁም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አሁን ላይ በኢትዮጰያ እና በሱዳን መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ተዘርግቶ ኃይል እየሸጥን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የኃይል ማመንጫዎች እየሰራች በቀይ ባህር በኩል ከግብጽ ጋርም በማገናኘት ወደ አውሮፓ ሃይል የመላክ ፍላጎት እንዳከላትም አክለዋል።
ይህንንም በርከት ያሉ ግድቦችን በመስራት የሚሆን እንጅ ባዶ ህልም አይደለም፤ የምእራቡ ዓለም እና ሌሎች ሀገራት አሁን ያለውን የውሃ ፖለቲካ አቁመው ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የኢትዮጵያ ትልቁ ህልም አምፖል አይቶ የማያውቀውን 60 በመቶ የሀገሪቱን ህዝብ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ማስቻል ነው ሲሉም ተናግረዋል።